Sunday, November 24, 2024
spot_img

የሕወሃት ኃይሎች ባለፈው እሑድ በውጫሌ ከተማ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ሰንዝረው 9 ሰዎችን መግደላቸው ተዘገበ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 9፣ 2014 ― በአማራ ክልል፣ በደቡብ ወሎ ዞን፣ በአምባሰል ወረዳ በምትገኘው ውጫሌ ከተማ የሕወሃት ኃይሎች በፈጸሙት የከባድ መሳሪያ ጥቃት ሁለት ወንድማማቾችን ጨምሮ በአጠቃላይ ዘጠኝ ሰዎችን መግደላቸውን ቢቢሲ የአምባሰል ወረዳ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሀብቴ መለሰን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

የአገር መከላከያ ሠራዊት በሽብርተኛነት ከተፈረጀው ሕወሓት ጋር እያካሄደ ያለው ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ሳምንታት የቀሩት ሲሆን፣ ጦርነቱ ወደ አፋርና አማራ ክሎች ተስፋፍቶ ይገኛል።

ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ መልሶ ባገረሸው ጦርነት ወቅት የሕወሓት ኃይሎች በውጫሌና በአፋር ክልል ጭፍራ አካባቢዎች ላይ በፈጸሙት የከባድ መሳሪያ ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን መንግሥት አሳውቋል።

እሑድ እለት በውጫሌ ተፈጽሟል የተባለውን ጥቃት በተመለከተ የአምባሰል ወረዳ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሀብቴ መለሰ ‹‹ወደ ከተማዋ ከባድ መሣሪያ ተተኩሶ የዘጠኝ ሰው ሕይወት አልፏል። ከአንድ ቤት ሁለት ወንድማማቾች ሞተዋል። መደበኛ ሥራ ላይ የነበሩ እና በመሸሽ ላይ የነበሩም ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል›› ብለዋል። በተጨማሪም አራት ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተው ሕክምና በመከታተል ላይ እንደሚገኙም አክለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እየተካሄደ ያለውን ጦርነት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ የሕወሃት ኃይሎች በአማራና በአፋር ክልል ውስጥ የሚገኙ አዋሳኝ አካባቢዎችን ዒላማ በማድረግ ‹‹ሰላማዊ ሰዎች ላይ ተቀባይነት የሌለው ጥቃት›› ፈጽመዋል ብሏል።

በጦርነቱ በሰዎች ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ከአምባሰል እንዲሁም በዙሪያዋ ካሉ ከሌሎች ወረዳዎች ጦርነቱን በመሸሽ ብዙዎች ወደ ደሴ ከተማ መሰደዳቸውን አቶ ሀብቴ ለቢቢሲ ገልጸዋል። በተጨማሪም ነዋሪዎች አሁንም እየተፈናቀሉ እንደሚገኙ እና በደሴ ዘመድ ወይም ጓደኛ የሌላቸው ሰዎች በረንዳ ላይ እንደወደቁ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ የተናገሩት አዲስ የተዋቀረው የኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ የህወሓት ኃይሎች በውጫሌና ጭፍራ አካባቢዎች ላይ ፈጸሙት ባሉት ጥቃት ከ30 በላይ ንጹኀን ሰዎችን መግደላቸውንና በርካቶችን መፈናቀላቸውን ገልጸዋል፡፡

እሁድ ጥቅምት 7፣ 2014 የሕወሓት ኃይሎች ወደ አካባቢው መግባትን ተከትሎ ብዙ ነዋሪዎች ሸሽተው እንደወጡ የኮምዩኒኬሽን ኃላፊው አስረድተዋል። አቶ ሀብቴ ከባድ መሣሪያው የተተኮሰበትን አቅጣጫ እንዲሁም ሰዓት በማጣቀስ ‹‹ከባድ መሣሪያው የተተኮሰው በህወሓት ነው›› ብለዋል።

ጥቃቱን አድርሷል በሚል ክስ የቀረበበት ሕወሓት በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ደረሰ ስለተባለው ጥቃት እስካሁን ድረስ ያለው ነገር የለም፡፡

በሌላ በከል ከሰሞኑ ባገረሸው ጦርነት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ወደ ትግራይ ክልል መቀመጫ መቐለ ከተማ የአየር ላይ ጥቃት መሰንዘሩ በትላናትናው እለት መነገሩም ይታወሳል፡፡

በትላናትናው ዕለት በመቀሌ ከተማ በሁለት ቦታዎች የተደረገው የአየር ድብደባ ኢላማዎች የመገናኛ እና የሚዲያ ማሰራጫ ጣቢያዎች እንደነበሩ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የሕወሃት መገናኛ ብዙሃን በጥቃቱ ንጹሐን ሰለባ ሆነዋል የሚሉ ሪፖርቶችን ያወጡ ቢሆንም፣ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን በወጣው ዘገባ ንጹሐን እንዳልተነኩ አመልክተዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img