Sunday, September 22, 2024
spot_img

የመተከል ዞን የጸጥታ ችግር የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ማስተጓጎሉ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ያለው የጸጥታ ችግር ባለመሻሻሉ የዞኑን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ማስተጓጎሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውኛል ብሎ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ አስነብቧል፡፡

በመተከል ዞን የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ እስካሁን ድረስ እልባት ባለማግኘቱ አሁን ላይ በተለይ የገጠሩ ማኅበረሰብን እንቅስቃሴ መገደቡን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ የተስተጓጎለው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ፣ የማኅበረሰቡን ኑሮ ፈታኝ እንዳደረገውም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

በዞኑ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር መሻሻል አለማሳየቱን ተከትሎ ዞኑ በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከመከላከያ በተጨማሪ የክልል ልዩ ኃይሎች በአካባቢው መሰማራታቸው የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ ነዋሪዎች እንደሚሉት በዞኑ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን የገጠሩን ማኅበረሰብ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ነፃነት ለወራት አስተጓጉሏል ብለዋል። ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ አሁን ላይ በአብዛኛው ከከተሞች ውጪ የሆኑ የዞኑ አካባቢዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እና የማኅበረሰቡ እንቅስቃሴ እንደተገደበ ነው።

የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ባለባቸው አካባቢዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በጸጥታ ኃይል የታጀቡ መሆኑም ተገልጿል። የታጣቂዎች ጥቃት ያስተጓጎለው የዞኑ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ግብዓት የሚቀርቡ ተሸከርካሪዎችን ጭምር መሆኑን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።

ከግልገል በለስ ወደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በሚወስደው መንገድ ታጣቂዎች አንድ አሽከርካሪ ገድለው ንብረት መዝረፋቸውን ተከትሎ፣ ለሕዳሴው ግድብ ግብዓት የጫኑ ተሸከርካሪዎች ከሳምንት በላይ መቆማቸው ነው የተነገረው። ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ የሚያገለግል ግብዓት የጫኑ ተሽከርካሪች ግልገል በለስን አልፈው መሄድ ባለመቻላቸው፣ እየተንገላቱ መሆኑን የዐይን እማኞች ገልጸዋል። “ጭነት ይዘው የቆሙ የተሽከርካሪ ሹፌሮች ከሳምንት በላይ በመቆማቸው እየተቸገሩ ነው፤ አንዳንዶቹ የአልጋ ገንዘብ አልቆባቸው፣ አልጋ አከራዮች እንዲተባበሯቸው ጠይቀን እየኖሩ ነው” ሲሉ የአይን እማኞቹን ጠቅሶ ዘገባው አመልክቷል፡፡

በመተከል ዞን የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከኹለት ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም፣ እስካሁን የንጹኃን ዜጎችን ሞትና መፈናቀል የሚያስቆም መፍትሔ እንዳልተገኘ የሚገልጹት የዞኑ ነዋሪዎች፣ መከላከያ በዞኑ ቢኖርም ችግሩን መቅረፍ አልቻለም ማለታቸው ተመላክቷል፡፡

ችግሩ እልባት ባለማግኘቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ በዘንድሮው የምርት ዘመን የግብርና ሥራ ባለማከናወኑ የሚቀጥለው ዓመት ከጸጥታ ችግር በተጨማሪ ለረሃብ አደጋ የሚጋለጥበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል ነው የተባለው።

በዞኑ የተሰማሩት የመከላከያ እና የክልሎች ልዩ ኃይሎች በንጹኃን ዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽምን ታጣቂ ኃይል የማያዳግም ዕርምጃ በመውሰድ ችግሩን ይቀርፋሉ ቢባልም፣ አስካሁን እንደተባለው እንዳልተፈጸመ ነው ነዋሪዎቹ የሚገልጹት። የተሰማራው የመንግሥት የጸጥታ ኃይል በዞኑ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ኃይል የሚያደርሰውን ጥቃት በኃይል ለማስቆም የሚያስችል አቅም ቢኖረውም፣ ዕርምጃ እየወሰደ አለመሆኑን ነዋሪዎች መታዘባቸውን ጠቁመዋል። በመሆኑም የፌደራሉ መንግሥት ችግሩን ተረድቶ ለዓመታት የዘለቀውን የዞኑን ማኅበረሰብ ችግር ለመፍታት ታጣቂ ኃይሉ ላይ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካሉት ሦስት ዞኖች በመተከል እና በካማሺ ዞኖች ያለው የጸጥታ ችግር መሻሻል ባለማሳየቱ፣ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በኹለቱ ዞኖች አለመካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ ሁለቱ ዞኖች አዲስ በተመሰረተው የሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት በሕዝብ የተመረጠ ተወካይ የላቸውም።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img