Saturday, September 21, 2024
spot_img

በምሥራቅ ወለጋና አካባቢው በንጹሐን ዜጎች ላይ ለሚፈፀመው ጥቃት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው ኢዜማ ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 2 2014 ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ትኩረት ተነፍጎታል ላለው በምሥራቅ ወለጋ እና አካባቢው በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት መንግስት በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

ፓርቲው ባወጣው መግለጫ በምሥራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ ሀሮ ቀበሌ እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤ ደንጎሮ እና ሆሮ ወረዳ – ሎሚጫ፣ ተሉሞቲ፣ ቦቶሮ፣ ቦራ፣ ወለጌ፣ ትጌ፣ ኮትቻ፣ ጋሬሮ፣ ጎርቴ፣ አርቡ ሲንታ፣ አርቡ ሶቴ፣ ገበርጉን 2ኛ፣ ኢዶ ቦቲ እና ሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ንፁሃን ዜጎች ላይ ‹‹ማንነታቸውን መሰረት አድርጎ እየተፈፀመ የሚገኘው አሰቃቂ ጥቃት ጊዜ እየጠበቀ እያገረሸ አሁንም የወገኖቻችንን ውድ ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል›› ብሏል።

በተደጋጋሚ ንፁሃን ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ከመጠቃታቸው በፊት ስጋታቸውን በአካባቢያቸው ላሉ የመንግሥት አካላት ሲገልፁ መቆየታቸውን ያስታወሰው ፓርቲው፣ የዞኑ አስተዳደር አባላት «በቁጥጥራችን ስር ነው፤ የሚያሰጋ ነገር የለም» እያሉ የብዙ ወገኖች ሕይወት መቀጠፉንም አመልክቷል፡፡

አካባቢው ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር መገናኛ መንገዶቹ ተቆፋፍረው በታጣቂዎች በመዘጋታቸው ምክንያት እንቅስቃሴ ተቋርጦ በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ህክምና፣ መድኃኒት፣ ሸቀጣሸቀጥ ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ከሆነባቸው መሰነባበቱንም በመግለጽ፣ የመሳሪያ ድምፅ እየሰሙ የሚውሉ ህፃናትም እጅግ ተሸብረዋል ነው ያለው።

ኢዜማ አክሎም ‹‹ንፁሃንን ለመታደግ በቦታው ያሉ የፌደራል የፀጥታ አካላት ቁጥራቸው ጥቂት በመሆኑ ሕዝቡን መታደግ ካለመቻላቸው ባለፈ እነሱም የጥቃቱ ሰለባ እየሆኑ እንደሆነ ከቦታው በደረሰኝ መረጃ አረጋግጫለሁ›› ያለ ሲሆን፣ የጥቃቱ መደጋገም እና ተመሳሳይነት የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት ማስጠበቅ ተቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን የሚገባው መንግሥት ለጉዳዩ የሚገባውን ያክል ትኩረት እንዳልሰጠው አመላካች ሆኖ እንዳገኘውም ገልጧል፡፡

በመሆኑም በተደጋጋሚ የሚደርሱትን ጥቃቶች ለማስቆም እና አጥፊዎችን ሕግ ፊት አቅርቦ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ለምን እንዳልተቻለ የክልሉ መንግሥት እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ማብራሪያ እንዲሰጡበት የጠየቀው ፓርቲው፣ ‹‹ከዚህ በፊት በአካባቢው ነዋሪዎች የደረሱ ከሰብዓዊነት ፍፁም የራቁ ግፎች አሁንም በአካባቢዎቹ የሚኖሩ ዜጎች ላይ ዳግም ሳይከሰቱ እርምጃ እንዲወሰድ እና ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ከሚደርስባቸው የደህንነት ስጋት ወጥተው ሰላማዊ የዕለት ከዕለት ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ዘላቂ መፍትሄ በአስቸኳይ መሰጠት እንዳለበት›› አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከቀናት በፊት እንዳሳወቀው በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ በመስከረም የመጀመሪያ ቀናት ብቻ 29 ሰዎች በታጣቂዎች የተገደሉ ሲሆን፣ የአካባቢው ሰላም በመድፍረሱም 40 ሺሕ ያህል ዜጎች ላለፉት ወራት ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img