አምባ ዲጂታል፣ እሑድ መስከረም 23፣ 2014 ― ሐሙስ መስከረም 20 በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሮ የነበረው ሕወሃት መቐለን ዳግም ከመቆጣጠሩ በፊት ያስተዳደረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊ የነበሩት አቶ አብርሃ ደስታ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተሰምቷል።
ሬውተርስ ስሜ እንዳይጠቀስ ብለውኛል ያላቸው የአቶ አብርሃን ጠበቃ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የቀድሞው ባለሥልጣን ለተጨማሪ ዘጠኝ ቀናት ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።
አቶ አብርሃ ደስታ በፍርድ ቤት በትግራይ ሕዝብ እና በፌዴራል መንግስት መካከል ጠብ በመጫር እንዲሁም ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ይዘው መገኘታቸው ተነግሯል ነው የተባለው።
አቶ አብርሃ ደስታ ቀድሞ በስፋት የሚታወቁት በትግራይ ክልል በሚንቀሳቀሰው የአረና ትግራይ ፓርቲ ከፍተኛ አመራርነታቸው ነው።
የአረና አመራሩ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት በነበሩት ባለፉት ቀናት ‹‹ትግርኛ መናገር እንደ ወንጀል ተቆጥሮ የትግራይ ተወላጆች ያለ ሀጥያታቸው ፍርድ ቤት ሳያውቃቸው ከያሉበት እየታፈሱ እየታሰሩ›› ነው የሚል እንዲሁም የጦርነቱን አስከፊነት የሚገልጹ፣ በቁጥጥር ስር የመዋላቸው ዜና ከመሰማቱ ከሰዓታት በፊት ደግሞ ‹‹ጦርነትን መደገፍ ባህል ሲሆን ስለ ሰላም መስበክ ነውር ይሆናል። ፀብ ካሸለመ ዕርቅ ያስነውራል። ስለ ሰላም የሚዘረጉ እጆች የተቀደሱ ናቸው። ሰላም ለሕዝባችን›› የሚል ጽሑፍ በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ አስፍረው ነበር።