አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ መስከረም 17፣ 2014 ― የቀድሞውን የሱዳን ፕሬዝዳንት ዑመር አል በሽርን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይ.ሲ.ሲ) አሳልፎ የመስጠቱ ጉዳይ በ ሱዳን ካቢኔ አባላት መካከል መከፋፈል እንደፈጠረ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መርያም አል ሳዲቅ አል ማህዲ ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮችን ባካተተው ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ውስጥ መከፋፈል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
“የአልበሽር ጉዳይ በዘ-ሄግ ወይስ በካርቱም በሚቋቋምና በአይ.ሲሰ.ሲ በሚመራ የፍርድ ሂደት ይዳኝ” የሚሉ ውይይቶች እንደነበሩ ያስታወሱት ሚኒስትሯ፣ የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልተቻለም ተናግረዋል፡፡
“የሽግግር ምክር ቤቱ በአል በሽር ብቻም ሳይሆን ግልጽ እንዲሆኑለት የሚጠይቃቸው የተለያዩ ጉዳዮች አሉ፤ በእኛ በሲቪል አመራሮቹ በኩል ደግሞ አልበሽርም ሆነ ሌሎች የሰብዓዊ ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩትን አሕመድ ሃሮን መሰል የቀድሞ ተጠርጣሪ ሚኒስትሮች ለአይ.ሲ.ሲ ይቅረቡ የሚል ግልጽ አቋም ነበረን”ም ነው ያሉት፡፡
ለእኛ “አልበሽርን አሳልፎ ለመስጠት ብቻም ሳይሆን የዳርፉር ሰለባዎች ፍትህ እንዲያገኙ ለማድረግ ቁርጠኝነቱ አለን፡፡ ሆኖምም አይ.ሲ.ሲ በአልበሽር አገዛዝ የተፈጸሙትን ወንጀሎች ሰፋ አድርጎ እንዲመረምር እና የፍርድ ሂደቱን ከ2002-2004 ባለው ጊዜ ብቻ እንዳይገድብ እንፈልጋለን። እንደ አለመታደል ሆኖም በምክር ቤቱ አባላት መካከል ይህን ጨምሮ ሌሎች ውሳኔዎች እንዴት ይተገብሩ በሚለው ላይ መኳኋን የለም”ም ብለዋል፡፡
“የግልበጣ ሙከራው በጦር ኃይሉ የውስጥ እና የውጭ አካላት የተቀናበረ ነው”- ጠ/ሚ አብደላ ሃምዶክ
በቅርቡ በሱዳን የተደረገውን ያልተሳካ መፈንቅለ መንግስት የተካሄደው በቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አል-በሽር ታማኝ ወታደራዊ መኮንኖች ነው ከመባሉ ጋር ተያይዞ አስታየታቸውን የሰጡት መርየም፣ ሙከራው “በሱዳን ውስጥ ብልጭ ያለውን እውነተኛ ዲሞክራሲ የሚያጨልም ነው” ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ ድርጊቱ በሱዳናውያን እንዲሁም በወታደራዊ መዋቅሩ መካከል መከፋፈሎች እንዳሉ ማመላከቱን ግን አለመሸሸጋቸውን አል ዐይን ዘግቧል።
ሱዳን ከሳምንታት በፊት የቀድሞ ፕሬዝዳንትዋ አልበሺርን ለዓለም አቀፉ የቆር ፍርድ ቤት አሳልፋ እንደምትሰጥ ማሳወቋ አይዘነጋም።