Sunday, October 6, 2024
spot_img

የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት መሪ አል ቡርሃን ሱዳንን ማንም በብቸኝነት ሊመራ አይችልም ሲሉ ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ መስከረም 12፣ 2014 ― የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት መሪ እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሌ/ጄ ዐብዱልፈታህ አል ቡርሃን ‹‹ሱዳንን ማንም በብቸኝነት ሊመራ አይችልም›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ አዛዡ ‹‹አምክነነዋል›› ያሉትን የትናንቱን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በማስመልከት ዛሬ በሰጡት መግለጫ ሙከራው የመከነው በጦሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ጦራችን ተገቢውን መሰረተ ልማት ትጥቅ አሟልቷል፤ ይህን አቅሙን ለማሳደግ እንዲጠቀምበትም እንፈልጋለን›› ብለዋል፡፡

ቡርሃን የጦሩ አንድነት መጠበቅና መጠናከር ለሱዳን አንድነት ዋስትና ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ማንም አካል ጦሩን ገለል ሊያደርገው እንደማይችል ነው ቡርሃን የገለጹት፤ ጦሩ የሃገሪቱ እና የአንድነቷ “ጠባቂ” መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ቡርሃን አክለውም የጋራ ወታደራዊ ልምምዶቹ ውስጣዊ አንድነታችንን አጠናክረውታል ያሉ ሲሆን‹‹›“ሱዳንን ሊያሸንፍ የሚችል ኃይል የለም›› ሲሉ ማናገራቸውን የአል ዐይን ዘገባ ያመለክታል፡፡ መሪው ከሽግግር ሂደቱ ገለል አድርጎ ሱዳንን በብቸኝነት ሊመራ የሚችል አካል እንደማይኖርም ገልጸዋል፡፡

አል ቡርሃን ትናንት ከግልበጣ ሙከራው በኋላ በደቡባዊ ካርቱም አል ሻጃራ አካባቢ የሚገኘውን የጦር ካምፕ ጎብኝተው፤ ከጦሩ አባላት ጋር መወያየታቸው ተነግሯል፡፡

በቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ህዝባዊ እና ሲቪል መንግስት እንዲመሰረት አይፈልግም፤ ስልጣኑን አሳልፎ ለመስጠትም ዝግጁ አይደለም በሚል እንደሚተችና በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ከሚመራው መንግስታዊ አካል ጋር ትልቅ ቅራኔ ውስጥ እንደሚገኝም ዘገባው አስታውሷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img