አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጳጉሜን 1፣ 2013 ― የሕይወት አድን እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል ያመሩ ከአንድ መቶ በላይ ተሸከርካሪዎች መቐለ መድረሳቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡
በትላንትናው እለት ወደ ክልሉ መቀመጫ ደርሰዋል የተባሉት ተሸከርካሪዎች፣ 3 ሺሕ 500 ሜትሪክ ቶን የሕይወት አድን ምግቦችን የያዙ መሆናቸው ነው የተነገረው፡፡
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሰሜን ኢትዮጵያ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ለመድረስ በቀጣይም ጥረቱን እንደሚቀጥል ገልጧል፡፡
ከቀናት በፊት በትግራይ ክልል የነበረው እርዳታ አቅርቦት ከተጠናቀቀ ሁለት ሳምንት እንደተቆጠረ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ግራንት ሌይቲ መግለጻቸው መነገሩ የሚታወስ ነው፡፡
አስተባባሪው ባወጡት መግለጫ አስፈላጊ የሆኑ የሰብዓዊ እርዳታዎችን ማቅረብ አለመቻሉ፣ የነዳጅ እና የጥሬ ገንዘብ እጥረት መኖሩ በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በትግራይ ክልል ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ብለውም ነበር፡፡
በትግራይ ክልል 90 በመቶ የሚሆነው ነዋሪ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልገዋል ያሉት አስተባባሪው፣ 400 ሺሕ ያህሉ ደግሞ በረሃብ አፋፍ ውስጥ ይገኛሉ ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በትላንትናው እለት ደርሰዋል የተባሉ የእርዳታ ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ ተሸከርካሪዎቹ የሚያልፉበት የአፋር ክልል የተሽከርካሪዎቹን ማለፍ በማረጋገጥ፣ የሰብአዊ ድጋፉ በክልሉ በኩል እንዲተላለፍ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር በቅርበት እየሰራ ስለመሆኑም ባወጣው መግለጫ አሳውቋል፡፡
የክልሉ መንግስት ‹‹ጁንታው›› ሲል የሚጠራው የሕወሓት ቡድን ‹‹በአፋር ላይ ወረራ በመፈፀም ህፃናትና ሴቶችን ቢገድልም የአፋር ህዝብና መንግስት ግን የተጋሩ ህፃናት እና ሴቶችን ህይወት ያድናሉ›› ብሏል፡፡
ሕወሃት በሐምሌ ወር መጨረሻ ክልሉን ወሰን ጥሶ በመግባት በፈንቲ ረሱ ጋሊኮማ በተባለ ቦታ ላይ ንፁሐን አርብቶ አደሮችን ህፃናት፣ ሴቶችና ሽማግሌዎችን እጅግ ዘግናኝ የሆነ ጭፍጨፋ ማካሄዱን ያስታወሰው የአፋር ክልል፣ ቡድኑ ‹‹ንፁሃን የአፋር አረብቶ አደር ላይ እያደረሰ ያለው ጭፍጫፋና ዘር ማጥፋት በቃ እንግዲህ ሊለው የሚገባው›› ራሱ የትግራይ ሕዝብ መሆኑንም አመልክቷል፡፡