አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 27፣ 2013 ― ሰሜን ኮሪያ ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጋ ቻይና ሰራሹን የኮቪድ 19 ክትባቶች ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወር መጠየቋን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የክትባት እጥረት በመኖሩ ሰሜን ኮሪያ የክትባት እርዳታው በወረርሽኙ በእጅጉ ወደ ተጎዱ ሀገራት እንዲዛወር መጠየቋን የድርጅቱ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
በኢኮኖሚ አቅማቸው ወደ ተዳከመ ሀገራት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ለማዳረስ በማለም በተዘረጋውና ኮቫክስ በተሰኘው መርሃ ግብር አማካኝነት ከተካተቱ የክትባት አይነቶች በቻይና የተሰራው የሲኖቫክ ክትባትም ተካተዋል።
እንደ ዓለም ጤና ድርጅተ መረጃ ከሆነ እስከ ተያዘው ወር ድረስ በሰሜን ኮሪያ በኮቪድ -19 የተያዘ አንድም ሰው አልተመዘገበም፡፡
በሀገሪቱ የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ጉንፋን መሰል በሆኑ በሽታዎችን የተያዙ 37 ሺህ 291 ያህል ሰዎች ምርመራ ተደርጎ ሁሉም ከኮቪድ 19 ነጻ ሆነው መገኘታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት በሳምንታዊ ሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።
ሰሜን ኮሪያ የኮቪዲ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ጥብቅ የመከላከያ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች። ሀገሪቱ በወርሽኙ ምክንያት ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ድንበራቸው ከዘጉ የመጀመሪያዎቹ ሀገሮች አንዷ ነበረች።
ሀገሪቱ ለቀረበላት የክትባቶችን እርዳታ ፊቷን ስታዞር ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በሐምሌ ወር ደቡብ ኮሪያ የሚገኝና ከሀገሪቱ የስለላ ተቋም ጋር ግንኙነት ያለው የምርምር ማህበር ክትባቶች የጎንዮሽ ጉዳቶችን በተመለከተ ያለውን ስጋት በመጥቀስ ሊበረከትላት የታሰበውን ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ የአስትራዜኒካ ክትባቶችን ውድቅ አድርጋለች።
ሰሜን ኮሪያ በኮቪድ 19 ክትባቶች ውጤታማነት ላይ ጥርጣሬ እንዳላት የምትገልጽ ሲሆን የሀገሪቱ ብሄራዊ ጣቢያ በአውሮፓና አሜሪካ የተሰጡ ክትባቶች ያስገኙትን አሉታዊ ውጤት እያሰሱ በተደጋጋሚ እንደሚዘግቡም ተሰምቷል።