አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ነሐሴ 22፣ 2013 ― በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረደ 10 ንጹኃን ዜጎቸ ባሳለፍነው ነሐሴ 20 በታጠቁ ኃይሎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውኛል ብሎ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
ታጣቂዎቹ ከቻግኒ ወደ ግልገል በለስ ከተማ 14 ሰዎችን ጭነው ሲጓዙ የነበሩ ሁለት አነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖችን በማገት በቡለን ወረዳ 10 ንጹኃን ዜጎችን መግደላቸው ነው የተነገረው፡፡
ከታገቱት 14 ንጹኃን መካከል ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች የተገደሉ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ አራት ሰዎች ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ስዓት ድረስ ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም ተብሏል፡፡ ከንጹኃን ዜጎች ሞት በተጨማሪ ታጣቂ ኃይሉ ኹለት የመከላከያ አባላትን ማቁሰሉ ነው የተነገረ ሲሆን፣ ግድያዉ ሲፈጸም ከመከላከያ አባላቱ በኩል ተኩስ ባለመኖሩ ጥቃቱን ከሰነዝሩት ተቃራኒ ኃይሎች ውስጥ የሞተ ሰው እንደሌለም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት “ጥቃቱን የፈጸሙት በቡለን ወረዳ ጥበቃ እንዲያደርጉ ኃላፊነት የተሰጣቸው፣ ነገር ግን አደራቸውን ቅርጥፍ አድርገው የበሉ የጉምዝ ሽፍታዎች ናቸው።” ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ታጣቂዎች የሚሰነዝሩት ጥቃት በየወቅቱ እየጨመረ በመሆኑ፣ የሞቱ ሰዎችን በግልጽ ማወቅ ባይቻልም በየቀኑ ሰዎች እንደሚገደሉ ተናግረዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል እና ከመተከል ዞን የሥራ ኃላፊዎች በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡