Monday, September 23, 2024
spot_img

በኤካ ኮተቤና ሚሊኒየም አዳራሽ ያሉ የጽኑ ሕክምና አልጋዎች ሙሉ ለሙሉ በሕመምተኞች ተይዘዋል ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ነሐሴ 21፣ 2013 ― የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ተጠባባቂ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ዮናስ ገብረእግዚያብሄር እንደገለጹት ካለፉት ሶስት ሳምንታት ጀምሮ በቫይረሱ ተይዘው ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው።

አሁን ላይ በቫይረሱ ተይዘው መተንፈስ ተስኗቸው ወደ ሆስፒታል የሚመጡት ሰዎች እንደ ከዚህ በፊቱ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው እና አዛውንቶች ብቻ አይደሉም የሚሉት ዶክተር ዮናስ፣ ወጣቶች እና ህጻናትም በቫይረሱ ተይዘው ጽኑ ህክምና እየተሰጣቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

በቫይረሱ ተጠቅተው ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ አሁን ላይ በኤካ ኮተቤ ሙሉ ለሙሉ የጽኑ ህክምና መስጫ አልጋዎች በታካሚዎች ተይዘዋል ሲሉ መናገራቸውን የአል ዓይን ዘገባ ያመለክታል።

የጽኑ ህክምና መስጫ አልጋዎች ሙሉ ለሙሉ መያዛቸውን ተከትሎም በየቀኑ በአማካኝ 10 ሰዎች አልጋ አጥተው እየተጠባበቁ መሆኑንም ዶክተር ዮናስ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ አሁንም እየተዘናጋ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ቀጣዮቹ ቀናት በዓላት የሚበዙበት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ህብረተሰቡ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ብለዋል።

የሚሊኒየም ኮቪድ 19 ህክምና ማእከል ኮሚውኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ በማዕከሉ የጽኑ ህክምና አልጋዎች ሙሉ ለሙሉ በታካሚዎች መያዙን አስታውቋል።

በየዕለቱ ህክምና ፈልገው ወደ ማዕከሉ የሚመጡ የቫይረሱ ተጠቂዎችን ለማስተናገድ ህይወታቸው የሚያልፉ ወይም አገግመው ወደ ቤታቸው ከሚሄዱ ሰዎች ብቻ በሚገኙ አልጋዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ማዕከሉ ገልጿል።

ከአምስት ሳምንታት በፊት በዚህ ማእከል የነበረው የታካሚዎች ቁጥር 12 የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰአት የታካሚዎች ቁጥር ወደ 158 ማሻቀቡንም አሳውቋል።

ከ158 ታካሚዎች ውስጥ 50 የሚሆኑት በከፍተኛ ድጋፍ እና በማሽን እገዛ ላይ ያሉ ታካሚዎች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ታካሚዎች ደግሞ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ የኦክሲጅን ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛልም ብሏል።

ይህ ሁኔታ የማእከሉን የጽኑ ህክምና አቅም እየፈተነው ሲሆን ከተለያዩ የጤና አገልግሎት ተቋማት እንዲሁም ከማህበረሰቡ ወደ ማእከሉ ለኮቪድ ጽኑ ህክምና እየተመሩ ያሉ ታካሚዎችን ለማገልገል ከቀን ወደ ቀን እየከበደው እንደመጣም ማዕከሉ አስታውቋል።

በመሆኑም ማስክን በትክክል ማድረግ እንዲሁም የእጅ ንጽህናን በአግባቡ መጠበቅ አሁንም ቢሆን ወደር የሌላቸው መፍትሄዎች ስለሆኑ ማህበረሰቡ ሳይዘናጋ እነዚህን እርምጃዎች እንዲተገብር አሳስቧል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img