አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 19፣ 2013 ― የደቡብ ዕዝ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የዕዙ የሰራዊት አባላት ሆነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ለተፈረጀው ህወሓት ቡድን ሲሰሩ ነበሩ በተባሉ የሰራዊት አባላት ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ መስጠቱ ተገልጧል፡፡
የሰራዊት አባላቱ የሰራዊቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች አደጋ ላይ የሚጥሉና የትግራይ ልዩ ሃይልን የሚያጠናክሩ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸው በችሎቱ መነሳቱ ታውቋል፡፡
በተለይም የሰራዊቱን ልዩ ልዩ ምስጢራዊ ሰነዶች ለትግራይ ልዩ ሃይል አሳልፈው በመስጠት፣ የሰራዊቱን ልዩ ልዩ ትጥቆች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዳይሰጡ ምስጢራዊ ቡድን በማደራጀትና መሳሪያዎቹን በማበላሸት ስራ ላይ ተሰማርተው እንደነበር በችሎቱ ተገልጿል፡፡
ወታደራዊ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በቀረቡባቸው ክሶች ላይ በትክክል መከላከል ያልቻሉ በመሆኑ ጥፋተኛ ናቸው ማለቱ የተገለጸ ሲሆን፣ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱንም የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግስት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጎዳዮች ቢሮ ዘግቧል፡፡