– የአካባቢው ባለስልጣናት የታጣዎቹን መረጃ ሐሰት ነው እያሉ ይገኛሉ
አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 13፣ 2013 ― ራሱን ኦሮሞ ነጻነት ጦር እያለ የሚጠራው እና መንግሥት ሸኔ በማለት በቅርቡ አሸባሪ ሲል የፈረጀው ቡድን በጉጂ ዞን የሚገኙ ቀበሌዎችን ተቆጣጠርኩ ቢልም የዞኑ አስተዳዳሪ ግን ሐሰት ነው ማለታቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በጉጂ ዞን በሚገኙት ጉሚ ኤልዳሎ እና ሊበን ተብለው በሚጠሩ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች ቡድኑ ከሕዝብ ጋር ውይይት እያካሄደ እንደሚገኘ ከቀበሌዎቹ ሸሽተው የወጡ የመንግሥት ሠራተኞች እንደነገሩትም የዜና ተቋሙ አስነብቧል፡፡
የጉጂ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ኡጎ ግን የቡድኑ ታጣቂዎች ‹‹በአንዳንድ ቦታዎች ሕዝቡን እያስገደዱ ለስብሰባ እያስወጣ ነው›› ሲሉ ይናገራሉ።
አቶ ታደለ ቡድኑ ከሚለው በተቃራኒ እርሳቸው በሚያስተዳደሩበት ዞን ውስጥ በታጣቂ ቡድኑ ቁጥጥር ሥር የገባ ቀበሌ አለመኖሩን ተናግረዋል። ‹‹ለጥቂት ደቂቃዎች በተገኙባቸው ቦታዎች ፎቶ እና ቪዲዮ በመቅረጽ አካባቢውን እንደተቆጣጠሩ ለማስመሰል ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያወጣሉ›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ጉሚ ኤልዳሎ ወረዳ ውስጥ በምትገኘው ቡልቡላ ቀበሌ ይሰሩ ነበሩ ሁለት የጤና ባለሙያዎች ባለፈው ሐሙስ የመንግሥት ኃይሎች ከአካባቢው መውጣታቸውን ተከትሎ ታጣቂዎች ቦታውን መያዛቸውን መናገራቸው በዘገባው ተመላክቷል፡፡
የጤና ባለሙያዎቹ ጨምረውም ታጣቂዎቹ ሐሙስ ዕለት ቀበሌውን ከተቆጣጠሩ በኋላ ዓርብ ዕለት ሰብሰባ ብለው የአካባቢውን ነዋሪ መሰበሰባቸውን ተናግረዋል።
በጉሚ ኤልዳሎ የሚገኙት መልካ ጉዳ፣ ቡልቡል እና ቦብ የተባሉ ቀበሌዎች እንዲሁም በሊበን ወረዳ ዱንጎ ቀበሌ በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ እና ታጣቂዎቹ የቀበሌዎቹን ነዋሪዎች ሰብስበው እንደነበር አንድ የጉሚ ኤልዳሎ ወረዳ የቀድሞ አመራር እንደነገሩት ቢቢሲ አመልክቷል፡፡
በትዊተር በተረጋገጠ እና ኦዳ ተርቢ በሚል ስም በተከፈተ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር በሚለው ቡድን ቃል አቀባይ ገጽ ላይ መንግሥት ሸኔ የሚለው ቡድን ጉሚ ኤልዳሎ ወረዳ ውስጥ ነው በተባለ ስፍራ ነዋሪዎችን ሰብስበው የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ለጥፏል።
ቢቢሲ ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በጉጂ ዞን ጉሚ ኤልዳኖ ወረዳ ቡልቡል ቀበሌ ወስጥ የጤና ባለሙያ የሆኑት ሰው ተናገሩት እንዳለው የመንግሥት ጸጥታ አካላት ከስፍራው መውጣታቸውን ተከትሎ ታጣቂዎቹ ባለፈው ሐሙስ ቀበሌዋን መቆጣጠራቸውን ያስረዳሉ።
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከሚኖሩባት ቀበሌ 20 ኪሎ ሜትር እርቆ በሚገኝ ቦታ ውጊያ ሲካሄደ እንደነበረ እና ቁስለኞች ለሕክምና ወደሚስሩበት የጤና ተቋም መጥተው መታከማቸውን ይናገራሉ።
ታጣቂዎቹ ሐሙስ ዕለት ቀበሌዋን ከያዙ በኋላ ዓርብ ዕለት ስበሰባ ሲጠሩ በቀበሌው እንደነበሩ የጤና ባለሙያው ይናገራሉ።
ቡልቡላ ቀበሌ ከዓመታት በፊት በተደረገ ቆጠራ ወደ 6ሺህ ገዳማ ነዋሪዎች እንዳላት የተመላከተ ሲሆን፣ የጤና ባለሙያው ግን የነዋሪው ብዛት ከ8ሺህ አስከ 10ሺህ እንደሚገመት ይናገራሉ።
የጉጂ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ኡዶ እርዳቸው ሸኔ ብለው የሚጠሩት ቡድን በጉጂ ዞን ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ ቢያረጋግጡም ቡድኑ በቁጥጥሩ ስር አውሎ የሚያስተዳድረው ቀበሌ አለመኖሩን ይናገራሉ።
‹‹እኛ በቁጥጥር ሥር ውሏል የሚባል ቀበሌ አናውቅም። ይህ ቡድን የሚያስተዳድረው ቀበሌ ስለመኖሩ አናውቅም፤ የለንም›› ማለታቸውን ነው የተመለካተው፡፡
ታጣቂ ቡድኑ በተለያዩ ቀበሌዎች ነዋሪዎችን አነጋግሯን መባሉን በመተለከተም፤ “. . . ሕዝቡ የታጠቁትን መሳሪያ ፈርቶ ካልሆነ በቀር እነሱ የሚሉትን ይቀበላል ማለት አይደለም” ይላሉ።
“ሕዝቡ ትዋሻላችሁ እያለ እያባረራቸው ነው። ስበሰባው ለውጥ አያመጣም” ብለዋል።
ታጣቂዎቹ ወደ አንድ አካባቢ ዘልቀው በመግባት ወይም የመንግሥት የጸጥታ ኃይል የሌለበት መንግድ ላይ ፎቶግራፍ በመነሳት በማኅብራዊ ሚዲያ ላይ እንደተቆጣጠሩ አድርገው ይለጥፋሉ እንጂ በአንድ ስፍራ አይቆዩም በማለት የዞኑ አስተዳዳሪ ያስረዳሉ።