አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 13፣ 2013 – የባልደራስ አመራሮችን ችሎት የሚመሩ ዳኞችን በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያዎች አሰራጭቷል የተባለው ጌጥዬ ያለው በቁጥጥር ስር መዋሉ ተነግሯል፡፡
ባልደራስ የተሰኘ የፓርቲ ልሳን አዘጋጅ ነበር የተባለው ጌጥዬ ያለው፣ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ጠበቃ አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ነግረውኛል ብሎ አሻም ቲቪ ዘግቧል፡፡
አቶ ጌጥዬ ችሎት የሚመሩት ዳኞችን አስመልክቶ የተለያዩ መረጃዎችን በማህበራዊ ትስስር ገፁ ጽፎ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ አንቀፅ 439 መሠረት ችሎት በመዳፈር ጥፋተኛ ስለመባሉ የተናሩት ጠበቃው፣ ነገ ነሐሴ 14፣ 2013 ውሳኔ ይሰጠዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
ችሎት በመዳፈር ጥፋተኛ የተባለው ጌጥዬ ያለው፣ ነሐሴ 4፣ 2013 በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ድረ ገጽ ላይ ‹‹ዋልጌ ዳኞች›› የሚል ጽሑፍ አስነብቧል፡፡