Saturday, November 23, 2024
spot_img

አፍጋኒስታን በታሊባን ቁጥጥር ሥር ወደቀች

– የአፍጋኒስታን ፕሬዝደንት አሽራፍ ጋኒ ታሊባን መዲናዋን መቆጣጠሩን ተከትሎ ወደ ጎረቤት አገር ሸሽተዋል

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ነሐሴ 10፣ 2013 ― አፍጋኒስታን ከዓመታት በኋላ ዳግም በታሊባን ቁጥጥር ሥር ወድቃለች፡፡ ታሊባን በከፍተኛ ፍጥነት በርካታ የአፍጋኒስታን አካባቢዎችን በመቆጣጠር ትላንት እሑድ በመዲናዋ ካቡል የሚገኘውን ፕሬዝደንታዊ ቤተ መንግሥት ይዟል፡፡

ይህንኑ ተከትሎም የአፍጋኒስታን ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒ ወደ ጎረቤት ኡዝቤኪስታን መሸሻቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ ከአሽራፍ ጋኒ ጋር ባንድነት ባለቤታቸው እና የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪያቸው ሸሽተዋል፡፡

ፕሬዝደንቱ በፌስቡክ ባስተላለፉት መልዕክት ደም መፋሰስን ለማስቀረት በሚል ከባድ ውሳኔ በመወሰን አገር ጥለው መውጣታቸውን ለአፍጋን ሕዝብ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም አሽራፍ ጋኒ አገሪቱን ጥለው መሸሻቸው በበርካቶች አስተችቷቸዋል መባሉን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ታሊባን አፍጋኒስታንን ተቆጣጥሯል መባሉን ተከትሎ የታሊባን ተዋጊዎች ፕሬዝደንታዊ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ሆነው የሚያሳይ ምስል የለቀቁ ሲሆን፣ አልጀዚራ የታሊባን ታጣቂዎች ከቤተ-መንግሥቱ አስተዳዳሪዎች ጋር ተገናኝተው የቤተ-መንግሥት ርክክብ ሲያደርጉ አሳይቷል።

በሌላ በኩል በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከካቡል ለመውጣት በሚያደርጉት ጥረት በሃሚድ ካርዛይ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከፍተኛ ግርግር እና ግራ መጋባት ተጋብተው ሲተራመሱ የሚያሳዩ የፎቶ መረጃዎችም ወጥተዋል፡፡

በአየር ማሪፈያው በሺዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች ቢገኙም በሥፍራው የነበሩት አየር መንዶች እና የኢሚግሬሽን ሠራተኞች ቁጥር ግን አነስተኛ ነበር ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም ሰዎች አውሮፕላን ለመሳፍር በሚያደርጉት ግፊያ በርካቶች መጎዳታቸው ተገልጿል።

በፍጋኒታን ጦርነት ዋንኛ ተወናይ የሆነው የአሜሪካ መንግሥት በካቡል ኤምባሲ የሚሰሩ ሠራተኞችን ወደ ሃሚድ ካራዛይ አየር ማረፊያ ማንቀሳቀሱን አስታውቋል።

ትላንት ቀን ላይ የአሜሪካ የጦር ሄሊኮፕተሮች ከኤምባሲው ወደ አየር ማረፊያው ሲመላለሱ ታይተዋል ነው የተባለው፡፡

አሜሪካ ዜጎቿን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት ወደ 6ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን ልካለች።

አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አውስትራሊያን ጨምሮ ከ60 በላይ አገራት የአፍጋኒስታን እና የሌሎች አገራት ዜጎች ከአፍጋኒስታን መውጣት ከፈለጉ ፍቃድ እንዲሰጣቸው በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል።
አፍጋኒስታንን ለቀው መውጣት ለሚፈልግ ለየትኛውም አገር ዜጋ ፍቃድ እንዲሰጥ ታሊባን ተጠይቋል።

ሌላኛዋ አገር ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ ፓርላማዋ በአፍጋኒስታን ጉዳይ እንዲመክር ጠቅላይ ሚንስትሯ ቦሪስ ጆንሰን የፓርላማ አባላትን መጥራታቸውን የአገሩ የዜና ወኪል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የታሊባንን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ የተሳሳት ስሌት ላይ ደርሰዋል በሚል እየተወቀሱ ስለመሆኑም ዘገባው አክሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img