– አስከሬናቸው ላይ በስለት የተወጋ ክፍል ታይቷል
አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ነሐሴ 7፣ 2013 ― ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 5 ምሽት ኅልፈታቸው የተሰማው፣ ልደቱ አያሌው እና ጃዋር መሐመድን ጨምሮ የበርካታ ፖለቲከኞች ጠበቃ የነበሩት ዐብዱልጀባር ሑሴን ድንገተኛ አሟሟት ውዝግብ ፈጥሯል፡፡
በትላንትናው እለት በአዳማ የቀብር ሥርዐታቸው የተፈጸመው የአቶ ዐብዱልጀባርን አሟሟት በተመለከተ እከሬናቸውን የመረመረው የምኒልክ ሆስፒታል እስካሁን በይፋ ያሳወቀው ነገር ባይኖርም፣ ሞታቸው በሰው እጅ ሳይሆን አይቀርም ያሉ ግን ቅሬታቸውን ከቀብር ሥርዐታቸው በኋላ ማሰማታቸው ነው የታወቀው፡፡
አምባ ዲጂታል በተመለከተው አስከሬናቸውን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በስለት የተወጋ የሚመስል እስከ አስር ሳንቲ ሜትር የሚገመት የጭንቅላቸው የኋላ ክፍል ስንጥቅ ሲደማ ይታያል፡፡
በቀብር ሥርዐቱ ላይ የተናገሩት የአስከሬን እጥበት አካሄደዋል የተባሉ ግለሰብ የጠበቃው አስከሬን ከእንብርት እስከ አንገት ድረስ መቀደዳዱንም ገልጸዋል፡፡
የአስከሬኑ ላይ ምርመራ ያደረገው ሆስፒታል በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ አለመስጠቱም ቅሬታ መፍጠሩ ነው የተነገረው፡፡
በጠበቃው አሟሟት ጉዳይ አዲስ ስታንዳርድ ትላንት ምሽት ይዞት በወጣው ዘገባ አቶ ዐብዱልጀባር ሞተው የተገኙት በአዳማ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 12 ሲሆን፣ ሰዐቱም ምሽት ከ1 እስከ 30 ባለው ጊዜ መሆኑን የቅርብ ጓደኛቸው መሐመድ ጂማ ተናግሯል፡፡
በአካላቸው ላይ ምንም ዐይነት የሚታይ ጉዳት እንዳልነበር የገለፀው መሐመድ፣ ቅድሚያ ወደ አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዳቸውንም ነው ያመለከተው።
በሌላ በኩል የአዳማ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ኃላፊ መኩሪያ ድንቁ በበኩላቸው ለፖሊስ ቃላቸውን የሰጡ ሰዎች ተናገሩ ብለው እንደገለጹት፣ ጠበቃው ሞተው ተገኝተዋል በተባለበት አካባቢ ቀድሞ ሰዎች ወደ ባለቤታቸው እንዲደውሉ ስልኳን እንደሰጡና ባለቤትየው ስኳር ወይም ከረሜላ ስጡት ማለቷንና በዚህም የጤናቸው ሁኔታ በጥቂቱ መሻሻሉን አመልክተዋል።
አክለውም ሌላ ጊዜ ጠበቃው ሕመም ሲያገኛቸው ወደ ሆስፒታል የሚወስዳቸው ባጃጅ ወደ ሪፍት ቫሊ ሆስፒታል ሊወስዳቸው ቢመጣም ወደ አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል እየተወሰዱ ባሉበት ሕይወታቸው ማለፉን የፖሊስን ምርመራ ጠቅሰው አመልክተዋል።
ኃላፊው በሌላ በኩል አቶ ዐብዱልጀባር ሕይወታቸው ያለፈው በሪፍት ቫሊ ሆስፒታል ነው የሚሉ መረጃዎች ቢኖሩም ከድምዳሜ ላይ አለመድረሳቸውን የገለፁ ሲሆን፣ የአዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ባለሞያዎች ምንም ዐይነት ጉዳይ እንዳልደረሰባቸው መግለጻቸውም ተመላክቷል።