Monday, October 14, 2024
spot_img

በጣና ሃይቅ 13 የሚደርሱ ሰዎች ያሳፈረች ጀልባ እንደተሰወረች ፖሊስ አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ሐምሌ 11፣ 2013 ― በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ 13 የሚደርሱ ሰዎችን አሳፍራ በጣና ሃይቅ ጉዞ የጀመረች አነስተኛ ጀልባ መሰወሯን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ምክትል ኮማንደር ቸርነት አስማረ ለኢዜአ እንዳሉት ጀልባዋ የተሰወረችው በወረዳው አዲሰጌ ድንጌ ተብሎ ከሚጠራ ቀበሌ አባን ላይ ጎጥ መነሻቸውን በማድረግ ወደ ጎርጎራ ወደብ ጉዞ ከጀመረች በኋላ ነው።

ተጓዥቹ ሐምሌ 9፣ 2013 ሌሊት ድንች ጭነው ጉዞ መጀመራቸውን ከቤተሰቦቻቸው መረጃው ለፖሊስ መድረሱን ገልፀዋል።

ተሳፋሪዎቹ ከ10 እስከ 13 እንደሚደርሱና አብዛኞቹም በስም ዝርዝር መለየታቸውን የገለፁት ምክትል ኮማንደሩ ተሳፋሪዎቹ ከመዳረሻው ጎርጎራ ወደብ እንዳልደረሱ መረጋገጡን ተናግረዋል።

ከትላንት እኩለ ቀን ጀምሮ በሁለት ቡድን የተዋቀረ የፖሊስና የባለሙያዎች ቡድን ፍለጋ እያካሄደ መሆኑን አመልክተው እስካሁን ምንም አይነት ፍንጭ ማግኘት እንዳልተቻለ አስታውቀዋል።

በዛሬው እለትም ፍለጋው መቀጠሉን ጠቁመው ተጓዦቹ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወይ በማዕበል ተወስደዋል፤ አለበለዚያም ከአቅም በላይ በሆነ ጭነት ጀልባዋ ሰምጣለች የሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱን አብራርተዋል።

ተጓዦቹ የተነሱበት ሰዓት ለሊት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፍለጋውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ጠቅሰው ከዚህ በኋላ ሰዎችን በህይወት የማግኘት እድሉ ጠባብ እንደሆነም አመልክተዋል።

ከመነሻው እስከ መዳረሻው ያለው የውሀ ላይ ጉዞ የ15 ኪሎ ሜትር ርቀት እንዳለው አመልክትው በፍለጋው የሚገኘውን ዝርዝር ውጤት በቀጣይ ህዝቡ እንዲያውቀው እንደሚደረግ ምክትል ኮማንደር ቸርነት ማስታወቃቸውን የዘገበው ኢቢሲ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img