Sunday, October 6, 2024
spot_img

ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሳ የደቡብ አፍሪካው ነውጥ እንዲነሳ ‘አስቀድመው የወጠኑ’ እንዳሉ ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሐምሌ 10፣ 2013 ― የደቡብ አፍሪካው ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሳ በመላው አገሪቱ የተነሳው ነውጥ የታቀደና ዴሞክራሲ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው አሉ።

የቀድሞው ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ መታሰራቸውን ተከትሎ በተነሳው አለመረጋጋት ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 212 ደርሷል። ለቀናት የመገበያያ ማዕከሎች ሲዘረፉ፣ ሲቃጠሉም ነበር። ይህም የምግብ እጥረት በማሰከተሉ ፖሊሶች መደብሮችን በተጠንቀቅ ለመጠበቅም ተገደዋል።

የዙማ ትውልድ ከተማ በሆነው ክዋዙሉ-ናታል አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ንብረት ተዘርፏል የተባለ ሲሆን፣ 800 ሱቆችም መዘረፋቸውን የከተማው ከንቲባ ተናግረዋል።

ራማፎሳ ከተማውን በጎበኙበት ወቅት ‹‹ይህ አለመረጋጋት እና ዝርፊያ እንዲከሰት አስቀድመው የወጠኑ እንዳሉ ግልጽ ነው። ያዘጋጁትና ያስተባበሩትም ሰዎች አሉ›› ብለዋል።

ፕሬዚደንቱ ነውጡ የደቡብ አፍሪካን ዴሞክራሲ ለማሰናከል ያለመ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

የረብሻው ቀስቃሾች ማንነት እንደታወቀ ቢገልጹም “እንከታተላቸዋለን” ከማለት በዘለለ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም።

የነውጡ መነሻ በሆነው ክዋዙሉ-ናታል የሚኖሩ ዜጎች ምግብ ለማግኘት ከጠዋት ጀምሮ ለመሰለፍ ተገደዋል። ብዙ ነዋሪዎች ቤተሰቦቻችንን ምን እንመግባለን የሚል ጭንቀት ውስጥ እንደገቡ ቢቢሲ ነግረውናል ብሎ ዘግቧል፡፡
ለቢቢሲ ገልጸዋል።

መንግሥት የምግብ አቅርቦት እንዳይስተጓጎል ለማድረግ እየሞከረ እንደሚገኝ አስታውቋል። ረብሻውን እንዲያረግብ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ተሰማርቷል። ፖሊስም ኦክስጅን፣ መድኃኒትና ሌሎችም መሠረታዊ አቅርቦቶች ሲጓጓዙ ጥበቃ እያደረገላቸው ነው።

ፕሬዘዳንት ራማፎሳ ለሕዝቡ በቴሌቭዥን ባደረጉት ንግግር፤ የምግብ እጥረት እንደሌለ ገልጸው፤ ዜጎች በስጋት ምግብ እንዳያከማቹ አሳስበዋል።

በአገሪቱ በተነሳው ነውጥ ከ2 ሺሕ 500 በላይ ሰዎች በነውጡ እጃችሁ አለበት ተብለው እንደታሰሩም አክለዋል።

በሙስና ወንጀል ለፍርድ የቀረቡት ዙማ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ባለማክበር የ15 ወራት እስር ሲፈረድባቸው ደጋፊዎቻቸው ነውጡን ቀስቅሰዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img