አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሐምሌ 5፣ 2013 ― በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ መተከል ዞን፤ ቡለን ወረዳ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ በተፈጠረ ግጭት ምክንያት በወረዳው የሰዓት ዕላፊ ገደብ ተጣለ። በቅዳሜው ግጭት ቢያንስ 14 ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሆስፒታል ምንጮች ነግረውኛል ብሎ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር አስነብቧል።
የቡለን ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በትላንትናው ዕለት ባሰራጨው “ጥብቅ ማሳሰቢያ”፤ በአካባቢው ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ድረስ ከጸጥታ ኃይሎች ውጭ ማንኛውም ሰው መንቀሳቀስ ተከልክሏል። ከትላንት እሑድ ሐምሌ 4 ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ እንደጀመረ የተነገረውን ይህን የሰዓት ዕላፊ ገደብ የተጣለው በመተከል ዞን በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የጸጥታ ችግር ለመቆጣጠር የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ነው።
ኮማንድ ፖስቱ ከሰዓት ዕላፊ ገደቡ በተጨማሪ ከከተፈቀደላቸው ሰዎች ውጭ ድምጽ ያለውም ሆነ ድምጽ አልባ መሳሪያዎችን ይዞ መንቀሳቀስ መከልከሉን የወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል። ክልከላዎቹን ተላልፎ የተገኘ ግለሰብ ላይ “ህጋዊ እርምጃ” እንደሚወሰድበት ኮማንድ ፖስቱ “ጥብቅ ማሳሰቢያ” ሰጥቷል ተብሏል።
እንደ ቢሮው መግለጫ ከሆነ ኮማንድ ፖስቱ እነዚህን ክልከላዎች ያስተላለፈው፤ በቡለን ወረዳ እና አካባቢው የተከሰቱ “የጸጥታ ችግሮችን” መነሻ በማድረግ፤ ሁኔታውን ከገመገመ በኋላ ነው። ሆኖም መግለጫው በአካባቢው ተፈጠሩ የተባሉ “የጸጥታ ችግሮችን” ምንነት ሳይጠቅስ ቀርቷል።
አራት የወረዳው ነዋሪዎች ግን ተፈጠረ የተባለውን የጸጥታ ችግር እና ያስከተለውን ጉዳት በዝርዝር አስረድተዋል። የጸጥታ ችግሩ የተከሰተው ባለፈው አርብ ከሰዓት አንድ የአካባቢው ነዋሪ “በጉሙዝ ታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው” ይላሉ።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቡለን ወረዳ ነዋሪ፤ የሟች ቤተሰቦች ወደ ቀብር እየሄዱ ባሉበት ወቅት ወደ ገበያ ከመጡ የጉሙዝ ተወላጆች ጋር ከተገናኙ በኋላ ግጭት መፈጠሩን ተናግረዋል። ከትላንት በስቲያ በነበረው በዚህ ግጭት “ቁጥሩ በውል ያልታወቀ ሰው ተገድሏል” ሲሉም አክለዋል።
በወረዳው የጸጥታ ችግር እንደነበር ያረጋገጡት አንድ የመንግስት ሰራተኛ፤ በግጭቱ 17 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ገልጸዋል። የሰዓት ዕላፊ ገደቡ የተጣለውም ቅዳሜ ጠዋት ከተፈጠረው ግጭት በኋላ መሆኑንም አስረድተዋል።
በቡለን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚሰራ የጤና ባለሙያ በበኩሉ፤ ቅዳሜ በነበረው ግጭት 14 ሰዎች መሞታቸውን ተናግሯል። በግጭቱ ዘጠኝ ሰዎች መቁሰላቸውን እና ከእነርሱ መካከል ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሶስት ሰዎች ወደ ፓዌ አጠቃላይ ሆስፒታል “ሪፈር” መባላቸውን የጤና ባለሙያው ይገልጻል።
የወረዳው ነዋሪዎች ከቅዳሜው ግጭት በኋላ በአካባቢው በርካታ ሰዎች እየታሰሩ ነው ይላሉ። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት የቡለን ወረዳ ነዋሪ፤ ከ150 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ተናግረዋል። በግል ስራ የሚተዳደሩት አንድ የወረዳዋ ነዋሪም “ትንኮሳ የፈጠረው ሳይሆን፤ ነዋሪው ህብረተሰብ በተለይ ወጣቱ ነው እየታሰረ ያለው” ብለዋል።