አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሐምሌ 3፣ 2013 ― ከቀናት በፊት በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር የዋሉ የአውሎ ሚዲያ እና ኢትዮ ፎረም ባልደረቦችን ቤተሰብ ማግኘት አለመቻሉን ጠበቃቸው አቶ ታደለ ገብረመድኅን ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
የሚዲያ ባለሙያዎቹ የተያዙት በፌደራል ፖሊስ መሆኑን እና በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ወቅት በተለምዶ ሜክሲኮ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርምራ ማዕከል እንደነበር ተናግረዋል።
ታሳሪዎቹን እስከ ባለፈው ሳምንት ዐርብ ሰኔ 25፣ 2013 ድረስ ቤተሰብ ሲጠይቃቸው እና ምግብ ሲያደርስ የነበረ ቢሆንም፣ ከዛ በኋላ ግን ‘ተለቀዋል እዚህ የሉም’ ተብለው፣ ቤተሰብ ሊያገኛቸው እንዳልቻለና ‹‹ፍርድ ቤትም እስካሁን አልቀረቡም›› በማለት ተናግረዋል።
የሚዲያ ባለሙያዎቹ ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ ከመደረጉም በላይ የተያዙበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንዳልተነገራቸው አቶ ታደለ ያስረዳሉ።
‹‹የባለሙያዎቹን እስር በተመለከተ ፖሊስ በአንድ መገናኛ ብዙኃን ሲጠየቅ ባለሞያዎቹ የታሰሩት ከአሸባሪ ቡድን ጋር ግንኙነት ስላላቸው ነው የሚል ምላሽ እንደሰጠ አንብቤያለሁ፤ ከዛ ውጪ ግን ለእኛ በግልጽ አልተነገረንም›› ሲሉም ጠበቃው አክዋል፡፡
‹‹ቤተሰብ በጣም ተጨንቆ ወደ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሄደው አቤቱታ አቅርበው ነበር። ሰኞ እና ማክሰኞ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብለን እየጠበቅን ነበር ግን ሳይቀርቡ ቀርተዋል›› ያሉት ጠበቃው፣ በአገሪቷ ሕጎች ላይ የዘፈቀደ እስር ሊኖር እንደማይገባ መስፈሩን እንዲሁም ደንበኞቻቸው በተያዙ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ ነበረባቸው በማለት የአገሪቷ ሕግ ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል ብለዋል፡፡
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ ባወጣው መግለጫ ከታሰሩት የሚዲያ ባለሞያዎች መካከል የአውሎ ሚዲያ 12 እንዲሁም የኢትዮ ፎረም ሚዲያዎቹ አበበ ባዩ እና ያየሰው ሽመልስ ይገኙበታል፡፡