Sunday, October 13, 2024
spot_img

የሄይቲውን ፕሬዝዳንት የገደሉት ቅጥረኛ የሆኑ የውጭ ዜጎች ናቸው ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሐምሌ 2፣ 2013 ― የሄይቲው ፕሬዝዳንት ጆቨኔል ሞይዝን የገደሉት 28 አባላት ያሉት ቅጥረኛ የገዳዮች ቡድን ነው ሲል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ከእነዚህ መካከል ሃያ ስድስቱ ኮለምቢያዊያን ሲሆኑ፣ ሁለቱ ደግሞ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ሄይቲያዊያን ናቸው ሲሉ የፖሊስ አለቃ ሌዎን ቻርልስ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

ሁለቱ አሜሪካዊያንን ጨምሮ 17 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ስምንቱ ደግሞ እየታሰሱ እንደሆነ ተሰምቷል።

በሕይወት ካሉት ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ ዋና መዲናዋ ፓርቶፕሪንስ ውስጥ ከፖሊስ ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ የሞቱ እንዳሉም የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡

የታጠቁ ሰዎች ጆቨኔል ሞይዝን ባለፈው ረቡዕ ነበር ወደ መኖሪያ ቤት ገብተው ጥቃት የፈፀሙት። በጥቃቱ ፕሬዝዳንት ጆቨኔል ሞይዝ ሲገደሉ፣ ባለቤታቸው ማርቲን ደግሞ ቆስለው ፍሎሪዳ ወደሚገኝ ሆስፒታል ለሕክምና ተወስደው አሁን መልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተሰምቷል።

ጥቃቱን ማን እንዳቀደውና ዓላማው ምን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ተጠባባቂው ፕሬዝደንት ክሎውድ ጆሴፍ እንደተናገሩት ከሆነ ግን የ53 ዓመቱ ፕሬዝደንት ሰለባ የሆኑት “ሥልጣን በጥቂት ሰዎች እጅ መሆኗን” መቃወም በመጀመራቸው ሳይሆን አይቀርም።

ሐሙስ ዕለት ፖሊስ ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል የተወሰኑትን ከእነ ጦር መሣሪያቸውና ፖስፖርታቸው ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርጓል።

የፕሬዝደንቱ ግድያ በአህጉረ አሜሪካ ድህነት የናጣት ሃገር በምትባለው ሄይቲ ተቃውሞ እንዲነሳ ያደረገ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ የ15 ቀናት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።

ምንም እንኳ የሄይቲ ሕገ መንግሥት ፕሬዝደንቱ ከሞቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ይሾማሉ ቢልም ዳኛው በቅርቡ በኮቪድ-19 ምክንያት መሞታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

ከዚህ በኋላ ማሻሻያዎች ተደርገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይምሩ የሚል ሐሳብ መጥቶ፣ አሪዬል ሄንሪ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቢሾሙም፣ እስካሁን ቃለ መሐላ አልፈፀሙም።

የተባበሩት መንግሥታት ደግሞ ምክትሉ ጆሴፍ በተጠባባቂ ፕሬዝደንትነታቸው እስከ ምርጫ ድረስ መቆየት አለባቸው ብሏል።

11 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሄይቲ 59 በመቶ ሕዝቧ ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖር መረጃዎች ያሳያሉ።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img