አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሰኔ 29፣ 2013 ― በአቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ስር ያሉ ተከሳሾች ጉዳያቸውን እየተመለከተ በሚገኘው ችሎት ፊት ለሦስተኛ ጊዜ ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡
ተከሳሾቹ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 29፤ 2013 በጠበቆቻቸው በኩል ለችሎቱ ባቀረቡት የጽሑፍ ማመልከቻ ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ በድጋሚ ማስታወቃቸውን ኢትዮጵያ ኢንሳደር ዘግቧል፡፡
ተከሳሾቹ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ፀረ ሽብርና ሕገ መንግስታዊ ወንጀል ችሎት ከዚህ ቀደም ሰኔ 21፣ 2013 ባስገቡት ማመልከቻ፤ ችሎት ላይ መገኘት ስለማይችሉበት ምክንያት በተመሳሳይ ሁኔታ መግለጻቸው ይታወሳል።
በዛሬው ማመልከቻቸው ደግሞ ‹‹ክርክሩ የፖለቲካ ክርክር ነው። የሚፈታውም በአስፈፃሚው አካል እንጂ በፍርድ ቤቱ አይደለም›› ማለታቸውን የተከሳሾችን ደብዳቤ ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት ጠበቃ ቱሊ ባይሳ ተናግረዋል።
ጠበቃ ቱሊ፤ ተከሳሾች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ከአንዴም ሁለት ጊዜ እንዳነጋገሯቸው ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። ሆኖም ተከሳሾቹ ‹‹ፍርድ ቤቱ የስርዓቱ አካል ስለሆነ፤ ፍርድ ቤት መቅረብ አንፈልግም›› ማለታቸውን ጨምረው አስረድተዋል። እነ አቶ ጃዋር ባለፈው ሳምንት በጻፉት ማመልከቻም ከዚህ በኋላ በችሎት ላይ የማይገኙት ‹‹በፍትህ ላይ በሚተወን ድራማ ላይ ተሳታፊ ላለመሆን›› ከውሳኔ ላይ በመድረሳቸው መሆኑን አስታውቀው ነበር።
ተከሳሾቹ ዛሬ እና ባለፈው ሳምንት ችሎት ፊት ያልቀረቡት በራሳቸው ውሳኔ ቢሆንም፤ በሰኔ 10፤ 2013 በነበረው ቀጠሮ ግን ችሎት ያልተገኙት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነበር። ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ የወሰነው ከምርጫው ጋር በተያያዘ ባለ የጸጥታ ስጋት ምክንያት እንደነበር መግለጹ አይዘነጋም።
የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዛሬው የችሎት ውሎው የተከሳሾችን የፍርድ ቤት አንቀርብም ማመልከቻ ለሁለተኛ ጊዜ ቢያደምጥም፤ ቀጣይ ክርክር ለማድረግ ተለዋጭ ቀጠሮ ከመስጠት ወደ ኋላ አላለም። በዚህም መሰረት ዐቃቤ ሕግ በእነ ጃዋር ላይ የቆጠራቸው ምስክሮች ያለባቸውን የደህንነት ስጋቶች በተመለከተ ክርክር ለማድረግ ለሐምሌ 21፤ 2013 ቀጠሮ ሰጥቷል። በቀጠሮው ቀን ተከሳሾች እንዲቀርቡም ትዕዛዝ ማስተላለፉን ዘገባው አመልክቷል።