Friday, October 11, 2024
spot_img

ኬኔት ካውንዳ በ97 ዓመታቸው አረፉ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 11፣ 2013 ― ዛምቢያን ከነጻነት ማግሥት አንስቶ ለ27 ዓመታት የመሩት ፕሬዝዳንት ኬኔት ካውንዳ በ97 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

የሚወዷቸው ‹ኬኬ› እያሉ በቁልምጫ የሚጠሯቸው ካውንዳ፣ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስትላቀቅ የመጀመሪያው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ነበሩ፡፡

ፕሬዝዳንቱ በሳንባ ምች በሽታ በመታመማቸው ሰበብ፣ በዛምቢያ ዋና ከተማ ሉሳካ ውስጥ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሕይወታቸው ማለፉን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡

ለተጨቆኑ በመቆም የሚወደሱት ካውንዳ፣ ከማህተማ ጋንዲ እንደተዋሱት በሚናገሩት የአመጽ አልባ ትግል ‹‹ቻ ቻ ቻ›› የተሰኘ ንቅናቄ ዘመቻ የመሩ ሲሆን፤ በአንጎላ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ በያኔዋ ሮዴሽያ ወይም ዚምባቡዌ የአናሳ ነጮችን አገዛዝ ተፋልመዋል፡፡

በተጨማሪም አንድ ልጃቸውን በኤች አይ ቪ ያጡት ካውንዳ፣ ኋላ ላይ ቫይረሱን ለመዋጋት በተደረጉ እንቅስቃሴዎን ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ካውንዳ በአንድ ወቅት ‹‹ቅኝ ገዢነትን እንደታገልነው ሁሉ አፍሪካን ሊያጠፋት ነው›› ያሉትን ቫይረስ እንዲገታ ታግለዋል፡፡

ኅልፈታቸውን ተከትሎ የዛምቢያ ፕሬዝዳንት ኤድጋር ሉንጉ እውነተኛ የአፍሪካ ምልክት ነበሩ ባሏቸው የቀድሞው የአገሪቱ መሪ ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ አገሪቱም የ21 ቀናት የሐዘን ጊዜ አውጃለች፡፡

በካውንዳ ኅልፈት ሐዘናቸውን ከገለጹት መካከል የአገሪቱ ዝነኛ የቀድሞ የእግር ኳስ ኮከብ ካሉሻ ቡዋሊያ፤ ካውንዳ በዛምቢያዊያን ላይ ያሳረፉት ተጽእኖ አወድሶ ጽፏል፡፡

ኬኔት ካውንዳ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል በትዳር ከተጣመሯቸው ቤቲ ካውንዳ 8 ልጆችን አፍርተዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img