አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሰኔ 5፣ 2013 ― በቅርቡ የቅድመ ኃይል ማመንጨት ሥራ ይጀምራል ተብሎ ለሚጠበቀው የሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ መስመሩን ዝግጁ እተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
በዚህም የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታው በተጠናቀቀው የዳሴ – ደዴሳ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተለያየ ምክንያት የተሰበሩትን ኢንሱሌተሮችን በአዲስ የመተካት ስራ መጀመሩም ነው የተነገረው፡፡
የምዕራብ ሪጅን ትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ቶማስ መለሰ፤ ኢንሱሌተሮቹን የመተካት ሥራው የተጀመረው በቅርቡ የቅድመ ኃይል ማመንጨት ሥራ ለሚጀምረው የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መስመሩን ዝግጁ ለማድረግ ነው ብለዋል።
ኢንሱሌተር የመቀየር ሥራው ከህዳሴ – ደዴሳ – ሆለታ ድረስ ከተዘረጋው መስመር መካከል እስከ ዲዴሳ ማከፋፈያ ጣቢያ ድረስ ባለው በሁለቱም የማስተላለፊያ መስመሮች (ሎት1 እና ሎት 2) በተተከሉ ምሶሶዎች ላይ የሚከናወን መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በመስመሩ ላይ በተካሄደለት የፍተሻ ሥራ መሠረት በሁለቱም መስመሮች ላይ ከተተከሉት 1 ሺሕ 535 ምሰሶዎች መካከል በ312 ምሰሶዎች ላይ የሚገኙ ኢንሱሌተሮችን በሌላ የመቀየር ስራ እንደሚከናወን ኃላፊው ጠቁመዋል።
በቀጣይ ከደደሳ ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ ሆለታ ማከፋፈያ ጣቢያ በተዘረጋው ባለ 500 ኪሎ ቮልት ማስተላለፊያ መስመር ላይ የተሰበሩ ኢንሱሌተሮችን በተመሳሳይ የመቀየር ሥራ እንደሚከናወን መነገሩን የዘገበው አል ዓይን ነው፡፡