Tuesday, October 8, 2024
spot_img

ኢትዮጵያ በቅንነት ሥራቸውን የሚሰሩ ጋዜጠኞችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 16፣ 2013 ― ኢትዮጵያ በቅንነት ሥራቸውን የሚሰሩ ጋዜጠኞችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

“ኢትዮጵያ ሃሳብን በነጻነት መግለጽንና የፕሬስ ነጻነትን በተመለከተ ያላትን ጽኑ አቋም ደጋግማ አስታውቃለች” ያለው ባለስልጣኑ፣ ሐሳብን በነጻነት መግለጽንና የፕሬስ ነጻነትን ጥበቃ በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት በክብር የተቀመጠ እሴት መሆኑን ገልጿል።

ለእነዚህ እሴቶች መጠበቅ የኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ያመለከተ ሲሆን፣ ቁርጠኝነቱ በተግባር የተተረጎመ ስለመሆኑንም አመልክቷል።

ለአብነትም ጋዜጠኞችና ፖለቲካ ከእስር መፈታታቸውንና በርካታ የለውጥ ተግባራት ባለፉት ሶስት አመታት ተከናውነው የሃሳብ ነጻነት ምህዳር እንዲሰፋ መደረጉን ጠቅሷል።

ቀደም ባሉት ዐመታት ሃሳብን በመግለጽና በፕሬስ ነጻነትን ላይ ገደብ የሚጥሉ እንቅፋቶች እንዲነሱ ተደርጎ ለአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች መረጃ የሚያገኙበት ምቹ መደላደል መፈጠሩን ገልጿል።

በአገሪቱ ውስጥ እንዲሰሩ ፈቃድ የተሰጣቸው 35 የውጭ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት 129 ቋሚ ነዋሪነት ፈቃድ ያላቸው ዘጋቢዎች እንዳሏቸው አመልክቷል።

ከዚህ ባለፈም በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ ለ82 የውጭ ጋዜጠኞች ጊዜያዊ ፈቃድ ተሰጥቶ ያለውን ሁኔታ መዘገብ የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸቱን አመላክቷል።

“እኛ ጠብቀን የነበረው የጋዜጠኝነት ስነ ምግባርን ከግምት ያስገባ በሙያ ላይ የተመሰረተ ዘገባ ነበር” ያለው መግለጫው፤ በጋዜጠኞቹ ጥንቃቄ የሚያሻቸው ጉዳዮች ላይ ተገቢው ጥንቃቄ ይደረግባቸዋል የሚል ግምት እንደነበረው አውስቷል።

በየትኛውም ዓለም እንደሚደረገው ወታደራዊ ዘመቻ በሚካሄድበት አካባቢ ገደብ እንደሚጣል ያነሳው መግለጫው፤ ፈቃድ የተሰጣቸው ዘጋቢዎችም ይህንን እውነታ አክብረውና ጠብቀው ይሰራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።

ነገር ግን የህግ ጥሰት ሲያጋጥም በየትኛውም የዓለም ክፍል እንደሚደረገው ባለስልጣኑ ህግን የማስከበር ሃላፊነቱን የመወጣት ግዴታ እንዳለበት ገልጿል።

በዚህም መሰረት የዓለም ዓቀፍ ተሞክሮን በመከተል በትብብር ለመስራት እንደሚሞክር አመልክቷል።

ስለሆነም ሃሳብን በነጻነት መግለጽንና የፕሬስ ነጻነትን በተመለከተ የያዘው አቋም የማይናወጥ መሆኑን ገልጾ፤ “አገሪቷም ሆነች ባለስልጣኑ በቅንነት ስራቸውን የሚሰሩ ጋዜጠኞችን ለማስተናገድ ዝግጁ ናቸው” ብሏል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img