Sunday, November 24, 2024
spot_img

በሆሮ ጉድሩ ወለጋ የተፈጸመ ጥቃትን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ ተፈናቅለዋል በሚል ለተሰራጨ መረጃ የዞኑ አስተዳዳሪ ‹ፋኖ› የተባለውን ቡድን ተጠያቂ አደረጉ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ግንቦት 14፣ 2013 ― በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን፤ አቤ ዶንጎሮ ወረዳ ወለጌ ቀበሌ ላይ ታጣቂዎች ባለፈው ማክሰኞ ግንቦት 10 ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ‹‹ሙሉ ለሙሉ›› ቀያቸውን ለቅቀው ተሰደዋል መባሉን የዞኑ አስተዳዳሪ አስተባብለዋል፡፡

በሥፍራው ደርሷል በተባለው ጥቃት ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረ ገጽ አነጋግሬያቸዋሁ ያላቸው የአዲስ አለም አካባቢ ነዋሪዎች ሦስት ሰዎች መገደላቸውን በመግለጽ፣ በመኖሪያ ቀያቸው አምስት መቶ ሰዎች ይኖሩባት እንደነበርና አሁን ግን ምንም አይነት ሰው እንደማይገኝ፣ ነዋሪዎችም ‹‹ወደ አጎራባች አካባቢዎች ሸሽተዋል›› ብለዋል፡፡

ሆኖም ግድያውን ያረጋገጡት የሆሮ ጉድሩ ዞን አስተዳዳሪ አቶ በቀለ ደቻሳ፣ ነዋሪዎች ‹‹ሙሉ በሙሉ ተፈናቅለዋል›› መባሉን ግን አልተቀበሉትም፡፡

‹‹የአካባቢው ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ ተፈናቅለዋል›› በሚል መነገሩን ‹‹ውሸት ነው›› ያሉት አስተዳዳሪው፣ ይህን ወሬ የሚያሠራጩት በአካባቢው ‹‹‘ፋኖ’ በሚል ሥም የተደራጁ ጽንፈኞች እና የእነሱ ተላላኪና ጀሌዎች ናቸው›› ሲሉ ቡድኑን ኮንነዋል፡፡

አስተዳዳሪው በተጎጂዎች ቁጥር ላይ ብቻ ሳይሆን ‹‹ከአካባቢው ተፈናቅለዋል በተባሉ የነዋሪዎች ብዛት›› እና ‹‹የጥቃቱ ኢላማ ናቸው›› በተባሉ ሰዎች ላይ በነዋሪዎች ከሚነገረው የተለየ መረጃ ሰጥተዋል።

በአካባቢው የተፈጠረውን ጥቃት ተከትሎ የተፈናቀሉ የአዲስ ዓለም አካባቢ ነዋሪዎች መኖሪያቸው ጥለው እንዲሸሹ ያደረጋቸው ‹‹ማንነት መሰረት ያደረገ ጥቃት›› እንደሆነ ቢናገሩም፤ የዞኑ አስተዳዳሪ ግን ‹‹ጥቃቱ ማንነትን መሰረት ያደረገ አይደለም›› ሲሉ ውንጀላውን ውድቅ አድርገዋል። ጥቃቱን የፈጸሙት ‹‹የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው›› የሚሉት አቶ በቀለ፤ ‹‹ሸኔ የአማራም፤ የኦሮሞም ጠላት ነው›› ሲሉ ጥቃቱ በሁሉም ላይ የተሰነዘረ መሆኑን ገልጸዋል።

ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በአቤ ዶንጎሮ ወረዳ መኖራቸውን የተናገሩ አንድ ግለሰብ መንግሥት ቸልተኛ ባይሆን ኖሮ ጥቃቱ አይፈጸምም ነበር ሲሉ መንግስትን ወቅሰዋል። ‹‹የመንግሥት ጥበቃ የለም። ጥቃት ከተፈጸመ እና ጥቃት አድራሾችም ከሄዱ በኋላ ነው የጸጥታ ኃይሎች የሚደርሱት›› ሲሉ ተችተዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች ለሕይወታቸው ‹‹ዋስትና›› የሚሰጣቸው አካል ባለመኖሩም፤ ወደ ቀያቸው ለመመለስ ስጋት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የሆሮ ጉድሩ ዞን አስተዳዳሪ ግን ‹‹በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ምንም አይነት አስጊ ሁኔታ የለም›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የጸጥታ እና የፖለቲካ መዋቅሩ ተደራጅቶ አካባቢውን የማረጋጋት ሥራ እየሰራ እንደሆነም ገልጸዋል። የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ እና የፌደራል ፖሊስ በስፍራው መሰማራታቸውን የሚናገሩት አስተዳዳሪው፤ ከአካባቢው ሚሊሺያዎች ጋር በመቀናጀት ጥበቃ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img