Tuesday, October 8, 2024
spot_img

እነ ስብሐት ነጋ አራት አዋጆች ላይ የሕገ መንግሥት ጥያቄ አቀረቡ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ግንቦት 11፣ 2013 ― በተጠረጠሩባቸው የተለያዩ ወንጀሎች ከጥር ወር 2013 ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ስብሐት ነጋ፣ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር)፣ አቶ ዓባይ ወልዱ፣ ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር)ን ጨምሮ 42 ተጠርጣሪዎች፣ ለተጠረጠሩባቸው የወንጀል ድርጊቶች በተጠቀሱባቸው አራት አዋጆች ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ፣ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲመራላቸው ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ግንቦት 9፣ 2013 ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛና ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በጠበቆቻቸው አማካይነት ባቀረቡት አቤቱታ እንደገለጹት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መጋቢት 2፣ 2013 ለፍርድ ቤቱ ክስ መሰል ማመልከቻ ጽፏል፡፡

በማመልከቻው ላይ የተዘረዘረው ክስ ተጣሰ ለተባለው ወንጀል የሕግ ድንጋጌ ሳይጠቀስ ነው፡፡ የሕግ ድንጋጌው ባይጠቀስም ፍርድ ቤቱ ሲመለከተው መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ክስ መሰል ማመልከቻ ያቀረበው ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በዝግ ችሎት እንዲሰሙ የሰጠውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ መሆኑን ጠቁመው፣ ነገር ግን ምስክሮቹ ከመስማታቸው በፊት፣ በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ማግኘት የሚገባቸውና ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረኑ አራት አዋጆች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 84 (2) እና በአዋጅ ቁጥር 798/2006 አንቀጽ 3 (2ሀ) እና 4 (2) ድንጋጌዎች መሠረት፣ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ እንዲልክላቸው በአቤቱታቸው አብራርተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ አከራክሮ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 13፣ 2013 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img