አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሚያዝያ 30፣ 2013 ― በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ሚያዝያ 25 ሌሊት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር የሆኑት የአቶ ዳውድ ኢብሳን ቤት ሰብረው የገቡት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት መሆናቸውን የአቶ ዳዉድ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ሽጉጥ ገለታ ለቪኦኤ ነግረውታል፡፡
እንደ ዶክተር ሽጉጥ ከሆነ የፖሊስ አባቱ የከተማው ፖሊስ አባላት መሆናቸውን ያወቁት ከመካከላቸው ኮማንደር ተስፋዬ ለማ የተባሉ አባል ይህንኑ በማረጋገጣቸው መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፣ ምሽት ስለነበር በመልክ እንደማይለዩዋቸው ነው የገለጹት፡፡
እነዚሁ የፍርድ ቤት ትእዛዝ አልያዙም የተባሉት የፖሊስ አባላት፣ በእለቱ ወደ ሊቀመንበሩ ቤት ዘልቀው የግቢውን ጠባቂዎች ትጥቅ ማስፈታታቸውን የሚናገሩት ከፍተኛ አማካሪው፣ በግቢው ይገኙ የነበሩ አራት የአቶው ዳውድን አጋዦች በቁጥጥር ስር ማዋላቸውንም አመልክተዋል፡፡
ከመጋቢት 24 አንስቶ በቤታቸው በቁም እስር ላይ እንደሚገኙ የሚነገረው አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ በአሁኑ ወቅት ጠባቂዎቻቸው ተነስተው፣ ወደ ቤታቸው መግባት እንደማይቻልም አማካሪያቸው የተናገሩ ሲሆን፣ በቤታቸው የመገናኛ ዘዴዎችም ተቋርጧል ነው ያሉት፡፡