አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሚያዝያ 29፣ 2013 ― በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ትናንት ሐሙስ ባወጣው መግለጫ ለኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ 65 ሚሊዮን ዶላር መልቀቁን በመግለጽ፣ ከገንዘቡ 40 ሚሊዮን ዶላር በትግራይ አስቸኳይ መጠለያ፣ ንጹህ ውሃ እና የጤና አገልግሎት ለማቅረብ፣ ወሲባዊ እና ጾታዊ ሁከትን ለመከላከል እና ለሰብዓዊ ምላሽ የቴሌኮምዩንኬሽን ድጋፍ ለማድረግ የታቀደ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ እንዳለው በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 16 ሚሊዮን ሰዎች ሰብዓዊ ዕገዛ የሚፈልጉ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚገመቱት በትግራይ ክልል የሚገኙ ናቸው።
በጉዳዩ ላይ የተናገሩት በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ዕርዳታ ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ ‹‹የኢትዮጵያውያን ሕይወት እና አኗኗር በድርቅ እየወደመ ነው፣ ሕፃናት በተመጣጠነ ምግብ እጦት እየተሰቃዩ›› መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹ስድስት ወራት ባስቆጠረው የትግራይ ግጭት ሰላማዊ ሰዎች የገፈቱ ተሸካሚ ሆነው ቀጥለዋል›› ያሉት ኃላፊው፣ ሴቶች እና ልጃገረዶች የአሰቃቂ ወሲባዊ ጥቃት ዒላማ ሆነዋል። ሚሊዮኖች በተለይ ሙሉ በሙሉ ግንኙነታቸው በተቋረጠ ገጠራማ አካባቢዎች መሠረታዊ ግልጋሎቶች እና ምግብ ለማግኘት እየተቸገሩ ነው። የሰብዓዊ ምላሽ አሰጣጡን አሁኑኑ ማሳደግ አለብን›› የሚል ጥሪ አቅርበዋል፡፡