Sunday, November 24, 2024
spot_img

በኦሮሚያ ክልል ያለው የእስረኞች ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ እንደሚያሳስበው ኢሰመኮ ገለጸ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሚያዝያ 28፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኅዳር 11፣ 2013 እስከ ጥር 4፣ 2013 ባለው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ያለውን የእስረኞችን አያያዝ ሁኔታ በተመለከተ በ 21 የተመረጡ ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ክትትል ማድረጉን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በጎበኛቸው የፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢና በአፋጣኝ ሊሻሻል የሚገባው እንደሆነ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

በፖሊስ ጣቢያዎቹ ብዙ ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ “በወቅታዊ ሁኔታ” የተጠረጠሩ ናቸው በሚል መታሰራቸውን፣ ከነዚህም አብዛኛዎቹ ምርመራ ሳይጀመርባቸው እና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በሕግ ከተቀመጠው ጊዜ በላይ ታስረው እንደቆዩ የሚያመላክቱ “አሳማኝ መረጃዎች ቀርበዋል” ሲል ኮሚሽኑ ጠቁሟል።

በተጨማሪም በበርካታ ፖሊስ ጣቢያዎች ዐቃቤ ሕግ በቂ መረጃ ባለማገኘቱ ምክንያት የ “አያስከስስም ውሳኔ” የተሰጠባቸው ወይም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሠረት መለቀቅ የነበረባቸው ተጠርጣሪዎች ‘ዋና ተሳታፊ ናቸው ወይም በሌላ ወንጀል ይፈለጋሉ’ በሚል ያለ አግባብ ታስረው እንዲቆዩ መደረጉንም ነው ሪፖርቱ የሚገልጸው፡፡

የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ኃላፊዎች “በወቅታዊ ሁኔታ” ተጠርጥረው የታሰሩ እስረኞች ጉዳያቸው የሚታየው በዞን እና በወረዳ ደረጃ በተቋቋሙ “የፀጥታ ምክር ቤቶች” መሆኑ፣ ብዛት ያላቸው ተጠርጣሪዎችን በሕግ ከመዳኘት ይልቅ የፖለቲካ (የአስተዳደራዊ) ውሳኔዎች ሰለባ እንዲሆኑ ማድረጉም ተጠቁሟል።

ክትትል በተደረገባቸው የፖሊስ ጣቢያዎች ከሚገኙት እስረኞች መካከል የተወሰኑት በፖሊሶች በሚያዙበት ወቅት እንዲሁም በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው መግለጻቸውን ያነሳው የኢሰመኮ ሪፖርት ፣ ለጊዜያዊ እና ቋሚ የአካል ጉዳት የተዳረጉ እስረኞች መኖራቸውን ይፋ አድርጓል። ኮሚሽኑ በተወሰኑ ቦታዎች “የኦነግ ሸኔ” አባል ወይም ደጋፊ ናቸው በሚል የሚፈለጉ “ልጆቻችሁን አቅርቡ” በማለት አባት ወይም እናትን የማሰር፤ “ባልሽን አቅርቢ” በማለት ሚስትን የማሰር ተግባር እንደሚፈጸም ከተለያዩ ታሳሪዎች አሳማኝ ምስክርነቶችን መቀበሉንም አንስቷል። እንዲሁም በተወሰኑ ቦታዎች ሰዎችን ያለ አግባብ በማሰር “የኦነግ ሸኔ አባል ናችሁ ብለን አንከሳችኋለን” በማለት በማስፈራራት ገንዘብ የመጠየቅ ሁኔታዎች መኖራቸውን የተመለከተ ቅሬታ ከእስረኞች መቅረቡንም ኢሰመኮ ገልጿል፡፡

ክትትሉ በተደረገባቸው በሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎች ሴት እስረኞች የነበሩ ሲሆን “ከእነዚህም መካከል የተወሰኑት እድሜያቸው ከ 5 ወር አስከ 10 ዓመት የሚሆናቸው ሕጻናት ልጆቻቸውን ይዘው የታሰሩ ናቸው” ብሏል የኮሚሽኑ ሪፖርት። በሌላ በኩል በወንጀል ነክ ጉዳዮች ተሳታፊ ናቸው በሚል ተጠርጥረው የሚታሰሩ ሕጻናት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 172 መሠረት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በዋስ እንዲለቀቁ ቢጠበቅም፤ በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ከ 9 እስከ 18 ዓመት የሚሆናቸው ሕጻናት አካለ መጠን ከደረሱ ሰዎች ጋር ተቀላቅለው በእስር ላይ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ አመልክቷል።

የኢሰመኮ የክትትል ቡድን በተመለከታቸው በአብዛኛዎቹ ፖሊስ ጣቢያዎች ተጠርጣሪዎች ንፅህናቸው ባልተጠበቀ እና በጣም በተጨናነቁ ክፍሎች ለጤና ጎጂ በሆነ መልኩ እንደሚያዙ፣ የምግብ አቅርቦት አለመኖሩን እንዲሁም የውሃ፣ የመጸዳጃ እና የሕክምና አገልግሎት አቅርቦት ችግር መኖሩንም ነው ያስታወቀው፡፡

የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተጠቀሱትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በተመለከተ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር የምርመራ ቡድን በማዋቀር የማጣራት ሥራ መሥራቱን ጠቅሶ ግኝቶቹን በማስተባበል ዝርዝር ምላሽ ስለመስጠቱም ኮሚሽኑ ገልጿል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ችግሮቹ በአፋጣኝ እንዲቀረፉ እና በእስረኞች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ የፖሊስ አባላት ተጠያቂ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img