አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ታኅሣሥ 15፣ 2014 ― አሜሪካ የአገር መከላከያ ሠራዊት ትግራይ ክልል አለመግባቱን በበጎ እንደምትቀበለው በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ በኩል አሳውቃለች፡፡
ቢሮው በትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረው ማስታወሻ፣ የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ላይ ጥቃቶችን እንዲያቆም ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ ጎረቤት አገር ኤርትራ ደግሞ ጦሯን ከኢትዮጵያ መሬት እንድታስወጣ በድጋሚ ጠይቋል፡፡
ለግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሌለው ያመለከተው የአሜሪካ መንግስት፣ ሁሉም አካላት ግጭቶችን በማቆም እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዲቆም፣ የሰብአዊ አቅርቦት ተደራሽነት እንዲፈቀድ እና ተፋላሚ አካላት ወደ ድርድር እንዲገቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ትላንት ሐሙስ ታኅሣሥ 14 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የመከላከያ ሠራዊት ከሕወሓት ባስለቀቃቸው አካባቢዎች እንዲቆይ መንግስት መወሰኑን መናገራቸው መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
ዶክተር ለገሠ በሕወሓት ኃይሎች የተያዙ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የሚገኙ አካባቢዎችን ለማስለቀቅ የተካሔደው ‹‹ዘመቻ ህብረ ብሔራዊ አንድነት›› መጠናቀቁን ይፋ ባደረጉበት ወቅት፣ ሠራዊቱ በያዛቸው ቦታዎች የሚቆየው ከዚህ ቀደም ወደ ትግራይ በዘለቀበት ጊዜ ተከስተዋል ያሏቸው ‹‹ችግሮች ዳግም እንዳያጋጥሙ›› መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከጠቀሷቸው መካከል የኢትዮጵያ መንግስት ከትግራይ ክልል ‹‹ወታደራዊ ትጥቆች እና ሠራዊቱን ለማንቀሳቀስ›› ያደረገውን ጥረት በተማጽኖ ያስቀየሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እና አጽያፊ ድርጊት ሲፈጸም መከላከል ቀርቶ ድርጊቱን ያላወገዙ ሆነው መገኘታቸውን፣ መከላከያ ሰራዊቱ በትግራይ ክልል ሕግ ለማስከበር እንቅስቃሴ ባደረገበት ጊዜ በመጀመሪያ አካባቢ የተባባሪነት መንፈስ ከህብረተሰቡ ቢታይም የኋላ ኋላ ግን በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደገና ከኋላ›› መወጋቱን እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስትን እና መከላከያ ሰራዊቱን ከእኩይ ሴራ እና ወጥመድ ለመከላከል የሚለው ይገኙበታል፡፡
በፌዴራል መንግስት እና በሕወሓት መካከል የሚካሄደው ጦርነት አስራ ሦስት ወራት አስቆጥሯል፡፡