Sunday, September 22, 2024
spot_img

የሕወሓት ኃይሎች የአማራና አፋር ክልሎችን መልቀቃቸውን ሰላም ለማምጣት ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ ጄፍሪ ፌልትማን ገለጹ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ታኅሣሥ 14፣ 2014 ― የሕወሓት ኃይሎች የአማራና አፋር ክልሎችን መልቀቃቸውን ሰላም ለማምጣት ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዑኩ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ገልፀዋል።

ፌልትማን ከዚህ ቀደም የፌዴራል መንግስትም ሆነ አገራቸው አሜሪካ የሕወሓት ኃይሎች አጎራባች አካባቢዎችን ለቀው እንዲወጡ መጠየቃቸውን አስታውሰው፣ አሁን ይህ ሁኔታ መሟላቱን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ይህ አጋጣሚ የኢትዮጵያን ሰላም ለማስፈን መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልፀዋል።

ባለፈው እሑድ የሕወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ ላኩት በተባለ ደብዳቤ ላይ ኃይሎቻቸው ከትግራይ ክልል ውጪ ከነበሩባቸው አጎራባች ክልሎች ‹‹ለሰላም ዕድል ለመስጠት›› ሲሉ ለቅቀው እንዲወጡ ማዘዛቸውን መግለጻቸው መነገሩ አይዘነጋም።

የሕወሓት መሪዎች ይህ ቢሉም የጠቅላይ ሚኒስትር ሐቢይ አሕመድ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ሥዩም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአፋር እና የአማራ ክልል ኃይሎች በጋራ ባካሄዱት ዘመቻ ከፍተኛ ድል በማግኘት የሕወሓት ኃይሎችን ከክልሎቹ ማስወጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ትላንት ምሽት በሰጠው መግለጫ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ኃይሎች ቀድመው ካስለቀቋቸው በተጨማሪ በርካታ ቦታዎችን በመቆጣጠር ወደ አላማጣና ኮረም እያመሩ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

ይህ ባለበት ሁኔታ የሕወሓት ኃይሎች የአማራና አፋር ክልሎችን መልቀቃቸውን ሰላም ለማምጣት ልንጠቀምበት ይገባል ያሉት ፌልትማን፣ ከዚህ ቀደም በጦርነቱ ጉዳይ ከፌዴራል መንግስት እና ከህወሃት መሪዎች ጋር ለመምከር ወደ ኢትዮጵያ ሲመላለሱ እንደነበር ይታወሳል።

በፌዴራል መንግስት እና በሕወሓት መካከል የሚካሄደው ጦርነት 13 ወራትን አስቆጥሯል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img