Friday, November 22, 2024
spot_img

የሕወሓት ኃይሎች ወደ ትግራይ ለማፈግፈጋቸው የድሮን ጥቃቶች አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጄነራል ጻድቃን ገለጹ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ታኅሣሥ 14፣ 2014 ― የሕወሓት ወታደራዊ መሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሌተናል ጀነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ይመሩታል የሚባለው ጦር ወደ ትግራይ ክልል ለማፈግፈጉ የድሮን ጥቃቶች አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጄነራል ጻድቃን ገለጹ፡፡

ሌተናል ጀነራል ጻድቃን፣ ይህን የተናገሩት የቢቢሲ ኒውስ አወር አዘጋጅ ቲም ፍራንክስ የሕወሓት መሪዎች ፖለቲካዊ ውሳኔ አሳልፈን ወደ ትግራይ ተመልሰናል ቢሉም ሪፖርቶችን ጠቅሶ ‹‹ተሸንፋችሁ ነው ያፈገፈጋችሁት›› ባላቸው ወቅት ነው፡፡

ለአዘጋጁ ‹‹ድሮን አንድ ምክንያት አይደለም አልልህም›› ያሉት ጻድቃን፣ ነገር ግን ብቸኛው ምክንያት አይደለም ሲሉ መልሰዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹ወደ አዲስ አበባ በምንገሰግስበት ጊዜ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሂደቶች ከወታደራዊ አካሄዳችን ጋር ሊጣጣሙ አልቻሉም›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹የዲፕሎማቲክ›› ያሏቸው ሁኔታዎች ‹‹በሚፈለገው መልኩ እየሄዱ›› እንዳልነበሩም ገልጸዋል፡፡

ጨምረውም በተለይ ‹‹ግዙፍ›› ያሉት ሠራዊታቸው ‹‹በስንቅና ትጥቅ ሙሉ ለማድረግ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ረዥም ርቀት በሚጓዙበት ጊዜ ለድሮን ጥቃት›› ተጋልጦ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡

ድሮኖችን ለማፈግፈጋቸው በአንድ ምክንያትነት የጠቀሱት ሌተናል ጀነራል ጻቃን ገብረተንሳይ፣ ከሳምንታት በፊት የሕወሓት ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ እየተጠጋን ነው ባለበት ወቅት ጦርነቱ እያለቀ ስለሆነ ከመንግስት ጋር ድርድር አይኖርም ሲሉም ተደምጠው ነበር፡፡

በአንጻሩ ባለፈው እሑድ የሕወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ ላኩት በተባለ ደብዳቤ ላይ ኃይሎቻቸው ከትግራይ ክልል ውጪ ከነበሩባቸው አጎራባች ክልሎች ‹‹ለሰላም ዕድል ለመስጠት›› ሲሉ ለቅቀው እንዲወጡ ማዘዛቸውን ገልጸዋል፡፡  

የሕወሓት መሪዎች ይህ ቢሉም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ሥዩም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአፋር እና የአማራ ክልል ኃይሎች በጋራ ባካሄዱት ዘመቻ ከፍተኛ ድል በማግኘት የሕወሓት ኃይሎችን ከክልሎቹ ማስወጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ትላንት ምሽት በሰጠው መግለጫ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ኃይሎች ቀድመው ካስለቀቋቸው በተጨማሪ በርካታ ቦታዎችን በመቆጣጠር ወደ አላማጣና ኮረም እያመሩ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

የኮሚኒኬሽን አገልግሎቱ የፀጥታ ኃይሎቹ በቆቦ ግንባር በአንድ በዋጃና ጥሙጋ በኩል ወደ አላማጣ ከተማ እንዲሁም በተኩለሽ በኩል ወደ መረዋና ኮረም እያመሩ መሆናቸውን ነው የገለጸው፡፡

በሌላ በኩል ለረዥም ጊዜ በሕወሓት ተዋጊዎች ቁጥጥር ስር የቆየችውን በአማራ ክልል የዋግ ኽምራ ብሔሰብ ዞን ዋና ከተማ፣ ሰቆጣን ጨምሮ አብዛኛውን አካባቢዎች ከተዋጊዎቹ በማስለቀቅ አካባቢዎቹ በመንግሥት ቁጥጥር ስር መግባታቸውን ገልጧል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img