አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ታኅሣሥ 12፣ 2014 ― የአማራ ክልል የሕወሓት ኃይሎች ይዘዋቸው በነበሩ አካባቢዎች በሰውና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ቡድን ማሰማራቱን አስታውቋል፡፡
ጥናቱን የሚያስተባብረው የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንሙት በለጠ፤ ከክልሉ መሥሪያ ቤቶች ብቻ 120 የሚጠጉ ባለሞያዎች የተሳተፉበትና የተለያዩ የሙያ ስብጥሮች ያሉት ቡድን በክልሉ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት ለማጥናት መሰማራት መጀመራቸውን ነግረውኛል ሲል ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
አቶ አንሙት እንደተናገሩት፤ በክልሉ የደረሰውን ውድመት የሚያጠናው ቡድኑ ጤና፣ ግብርናና ትምህርትን ጨምሮ 16 መሥሪያ ቤቶችን፣ 10 ዩኒቨርስቲዎችን እንዲሁም የፌደራል ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲን ያሳተፈ ነው።
ጥናቱ የሚከናወነውም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከሕወሓት ኃይል በማስለቀቅ በተቆጣጠሯቸው በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ወሎ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በሰሜን ጎንደርና በደቡብ ጎንደር ዞኖችና ሁለት ከተሞች ነው።
አቶ አንሙት የጥናቱ ዋና ዓላማ በሕወሓት ኃይሎች ተይዘው በነበሩ የክልሉ ዞኖችና ከተሞች በሰውና በንብረት ላይ የደረሰውን ትክክለኛ የጉዳት መጠን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማጥናት ለመልሶ ማቋቋም፣ ታማኝና ተጨባጭ ማስረጃን በማደራጀት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ እንዲሁም አጥፊውን ተጠያቂ ለማድረግ የሚውል እንደሆነ አብራርተዋል።
ባለፈው ዓመት በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ የሕወሓት ኃይሎች በርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎችን ተቆጣጥረው መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
ኃይሎቹ ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን በመስፋፋት ወደ አዲስ አበባ ለመጠጋት የሞከሩ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጦሩን ለመምራት ወደ ግንባር መዝመታቸውን ተከትሎ በአጭር ጊዜ በርካታ ከተሞች በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ውለዋል።
የሕወሓት ኃይሎች ተቆጣጥረው በቆዩባቸው አካባቢዎች በሰዎች፣ በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በአየር ማረፊያ፣ በሙዚየምና ታሪካዊ ቦታዎች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም በሌሎች የመንግሥት ተቋማትና መሠረተ ልማቶች ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሳቸው ተዘግቧል።