Sunday, September 22, 2024
spot_img

የሕወሓት ሊቀመንበር ለአንቶንዮ ጉቴሬዝ ደብዳቤ ጻፉ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ታኅሣሥ 11 2014 ― ከፌዴራል መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኘው የሕወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚኤል ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ ደብዳቤ ሰደዋል፡፡

ሊቀመንበሩ ፊርማቸው ባረፈበትና የትግራይ ሕዝብ እና መንግሥት ወክለው እንደጻፉት በገለጹበት ደብዳቤ፣ በአሁኑ ወቅት ባለፉት አስራ ሦስት ወራት የትግራይ ሕዝብ እያለፈበት ነው ያሉትን ‹‹ሰቆቃ›› ዘርዝረዋል፡፡

የሊቀመንበሩ ደብዳቤ የመጣው የፌዴራል መንግስት ከሰሞኑ በሰነዘረው ጥቃት በሕወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩትን ወልዲያ እና ቆቦን ጨምሮ በርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎችን መቆጣጠሩን ካስታወቀ በኋላ ነው፡፡

የትግራይ ሕዝብ በየእለቱ ከሰማይ በሚለቀቀቅ የድሮን ጥቃት እየተሸበረ እንደሚገኝ የገለጹት ዶክተር ደብረጽዮን፣ በአሁኑ ጊዜ የትግራይን ድንበር ተሻግሮ የሚገኘውን ሠራዊታቸውን እንዲመለስ ትእዛዝ ማስተላለፋቸውን አመልክተዋል፡፡

ደብረጺዮን የትግራይን ድንበር ተሻግሮ የሚገኘውን ሠራዊታቸውን እንዲመለስ ትእዛዝ ማስተላለፋቸውን ቢገልጹም፣ አለመሸነፋቸውና አሁንም በሠራዊቱ ችሎታ መተማመን እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡ አያይዘውም ያሳለፉት ውሳኔ ለሰላም በር የሚከፍት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ንጹንን የመከላከል ግዴታውን መወጣት እንዳቻለ የሚገልጸው የሊቀመንበሩ ደብዳቤ፣ በቀጣይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማድረግ አለበት ያለውን አስቀምጧል፡፡ ከነዚህ መካከል ከሰብአዊ አቅርቦት ውጪ ወደ ትግራይ የሚደረግ ማንኛውም በረራ ላይ እግድ እንዲጣል እና በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲጣል የሚሉትን ዘርዝሯል፡፡

ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ለአንቶንዮ ጉቴሬዝ በጻፉት ደብዳቤ ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሔ እንደሌለው ጠቅሰዋል፡፡

ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለተመድ ዋና ጸሐፊ በጻፉት ደብዳቤ ድንበር ተሻግረን የያዝናቸውን መሬቶች ወታደሮቻችን ለቀው እንዲወጡ ትእዛዝ አስተላልፈናል ቢሉም ከመንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሌላ መረጃ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሑሴን መንግስት የውስጥ ጉዳዮችን በንግግር ለመፍታት በቅርቡ ሁሉን አካታች ብሔራዊ ውይይት የማድረግ እቅድ እንዳለው ለአናዶሉ ኤጀንሲ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ውይይቱ ሕወሓትን ያሳትፋል ወይ የተባሉት አቶ ሬድዋን፣ ለመናገር እንደሚቸግር ጠቁመው፣ ሕወሓት ብቸኛው የትግራይ ሕዝብ ወኪል አለመሆኑንም አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አገራዊ ምክክር መድረክ እንዲመራና እንዲያመቻች በሚል አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመቋቋም ላይ እንደሚገኝ መገለጹ አይዘነጋም፡፡

በቅርቡ እንደሚቋቋም ለሚጠበቀው ኮሚሽን ከሕዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶችና ከሲቪል ማኅበራት ኮሚሽነር ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦች ተጠቁመው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የሚሾሙ ስለመሆናቸው ተደንግጓል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img