Sunday, October 6, 2024
spot_img

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካገዳቸው ሠራተኞቹ መካከል የተወሰኑትን እግድ አነሳ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ታኅሣሥ 9 2014 ― ባለፈው ወር የመጀመሪያ ቀናት 422 ሠራተኞቹን በደንብ ጥሰት ያገደው መንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰበአመራር ደረጃ ካሉ ሠራተኞች ውጪ እግዱን አንስቷል፡፡

ሠራተኞቹ በወቅቱ የታገዱት ባንኩ ላልፈቀደው ሌተር ኦፍ ክሬዲት የመርከብ ጭነት ክፍያ ለደንበኞች በመፈጸም ተጠርጥረው ነበር፡፡ ሠራተኞቹ ሲታገዱ አብሮ የኅዳር ወር ደመወዛቸው መያዙም መነገሩ አይዘነጋም፡፡

የእንግሊዝኛው ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው፣ በአቶ ተክለወልድ አጥናፉ የሚመራው የባንኩ ቦርድ ባደረገው ስብሰባ፣ የበታች ሠራተኞችን አስር በመቶ ደመዛቸውን ቀጥቶ በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እግዱን አንስቷል፡፡

የነዚህ ሠራተኞች እግድ መነሳቱን ተከትሎ አብዛኞች ወደ ሥራ መመለሳቸውን ያመለከተው ዘገባው፣ የአመራሮቹ እግድ አለመነሳቱን ከመግለጽ ውጪ የተላለፈባቸው ውሳኔ ስለመኖሩ የጠቀሰው ነገር የለም፡፡

አንጋፋው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 422 ሠራተኞችን ሲያግድ፣ በዘርፉ ያልተለመደ ነው በሚል መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡

አሁን እግድ ከተነሳላቸው መካከል አንዳንድ ሠራተኞች ዳያስፖራ አካውንት ለከፈቱ ደንበኞች፣ ከተገልጋዮቹ የውጭ ምንዛሪ ሒሳብ በመቀነስ፣ የመርከብ አገልግሎት  ክፍያዎችን መፈጸም ቢኖርባቸውም፣ በተቃራኒው በብር አስገብተው ባንኩ በዶላር እንዲከፍል በማድረግ የተጠረጠሩም ነበሩ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ ሰኔ 17፣ 2002  ያወጣውን መመርያ በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማናቸውም በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ተጭነው ለሚገቡ የገቢ ዕቃዎች የሚከፈል የጭነት ክፍያ፣ በውጭ ምንዛሪ እንዲሆን በተመሳሳይ ወቅት ለሠራተኞቹ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።

ሠራተኞችም የውጭ ምንዛሪውን ተመጣጣኝ ገንዘብ ከደንበኞች ላይ በመሰብሰብ፣ በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት ስም በተከፈተው ሒሳብ ገቢ እንዲያደርጉና  ድርጅቱ ወደሚፈልገው አገር ባንክ በውጭ ምንዛሪ እንዲያስተላልፉ ታዘው ነበር። ነገር ግን የጭነት ክፍያዎችን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል መፈጸም የሚችሉት፣ በባንኩ በኩል ከውጭ ዕቃ እንዲያስመጡ ፈቃድ የተሰጣቸው መሆኑ ተጠቁሟል።

ከ60 ሺሕ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች ያሉት ንግድ ባንክ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመርያ ሦስት ወራት 6.8 ቢሊየን ብር ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን፣ 30.5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አግኝቷል። ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ትርፉ የ122 በመቶ ዕድገት ሲያሳይ ገቢው በ92 በመቶ አድጓል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img