Sunday, September 22, 2024
spot_img

ኢትዮጵያ በተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት የተላለፈውን ውሳኔ እንደማትቀበለው መንግሥት በድጋሚ አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ታኅሣሥ 9 2014 ― መንግስት በትላንትናው እለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በትግራዩ ጦርነት የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ገለልተኛ መርማሪ ኮሚሽን ለማቋቋም ያሳለፈውን ውሳኔ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው አስታውቋል፡፡

በስብሰባው ላይ እንዲቋቋም እውቅና የተሰጠው በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጸሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና በደሎችን የሚመረምረው ዓለም አቀፍ ኮሚሽን፣ ጥቅምት 24፣ 2013 ጀምሮ በሁሉም ወገኖች ተፈጽመዋል የሚባሉ የዓለም አቀፍ ሕጋግት ጥሰቶችን የመመርመር ኃላፊነት ተጥሎበታል።

ነገር ግን መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ባወጣው መግለጫው፣ የተመድ ሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በጥቂቶች ፖለቲካዊ አላማን ለማራመድ ሲውል መታዘብ ኢትዮጵያን ማሳዘኑን ገልጧል፡፡

የምክር ቤቱ ስብሰባ በትግራይ ጦርነት ከተመድ ሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ጋር ምርመራ ያደረገው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እንዳይካሄድ በደብዳቤ ቢጠይቅም ወደ ደጎን በመግፋት መሆኑንም ጭምር ያስታወሰው መግለጫ፣ ይህ ተግባር በአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት እንደ አማራጭ መወሰዱንም ጠቅሷል፡፡   

መንግስት ልዩ ስብሰባውን እና የተላለፈውን ውሳኔ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት፣ ሉአላዊነት እና የፖለቲካ ነጻነት የሚጋፋ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

የተመድ ሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በትላንት ስብሰባው ዓለም አቀፍ መርማሪ ኮሚሽን ለማቋቋም የወሰነው በ21 የድጋፍ ድምጽ፣ በ15 ተቃውሞ እና በ11 ድምጸ ተዓቅቦ ነው፡፡

የውሳኔ ሐሳቡን ከተቃወሙት መካከል የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆኑት ኤርትራ እና ሶማሊያን ጨምሮ ቡርኪና ፋሶ፣ ካሜሩን፣ ኮትዲቯር፣ ጋቦን እና ናሚቢያ ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ቻይና፣ ሩሲያ እና ህንድም የኮሚሽኑን ማቋቋም ጨምሮ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እና በደሎችን የሚያወግዘውን የውሳኔ ሐሳብ ከተቃወሙት መካከል ተገኝተዋል፡፡ በአንጻሩ ሌላኛዋ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሱዳን በውሳኔ ሐሳቡ ድምጽ ከመስጠት ታቅባለች፡፡

በዚሁ ልዩ ስብሰባ ወቅት የምክር ቤቱ አባል የሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ካውንስሉ ልዩ ስብሰባ መጥራቱን እንደሚቃወሙት በጋራ አስታውቀው የነበረ ሲሆን፣ ቡድኑ ኢትዮጵያን አስመልክተው ለምር ቤቱ አዲስ የውሳኔ ሃሳብ ያቀረቡ አካላት የውሳኔ ሐሳባቸውን እንደገና እንዲያጤኑት በስብሰባው ላይ አስተጋብቷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img