Monday, October 7, 2024
spot_img

የትግራይ ዓለም አቀፍ ካህናት ዘ ኦርቶዶክስ የተሰኘ ማኅበር ከኢትዮጵያ ሲኖዶስ ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋርጫለሁ አለ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ታኅሣሥ 7፣ 2014 ― የትግራይ ዓለም አቀፍ ካህናት ዘ ኦርቶዶክስ የተሰኘ ማኅበር ከኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋርጫለሁ ሲል በደብዳቤ አሳውቋል፡፡

ማኅበሩ ኅዳር 30፣ 2014 በጻፈውና ይፋ በተደረገ ደብዳቤው፣ ለውሳኔው ምክንያት አድርጎ ያስቀመጠው ባላፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የውስጥና የውጭ ‹‹የጥፋት›› ያላቸው ኃይሎች በትግራይ ሕዝብ ላይ፣ በሃይማኖት ኣባቶች፣ በጥንታዊያን ገዳማት ወ አድባራት እንዲሁም ቅርሶች ላይ አከናውነውታል ባለው ‹‹ጭፍጨፋ እና ውድመት›› የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ‹‹ከኦርቶዶክሳዊ ስነ ምግባር እና ኃላፊነት ባፈነገጠ መልኩ›› የጥፋቱ ተባባሪ እና አስፈጻሚ ሆኖ በማግኘቱ መሆኑን ገልጧል፡፡

ማኅበሩ በደብዳቤው ከሲኖዶስ ጋር ለመለያየት የወሰነበትን ‹‹ታሪካዊ እና ታላቅ›› ሲል የጠራውን ውሳኔ የወሰነው ‹‹በስሜት እና በወቅታዊ ሁኔታ ተገፋፍተን›› አይደለም ብሏል፡፡  

የትግራይ ዓለም አቀፍ ካህናት ዘ ኦርቶዶክስ የተሰኘው ማኅበር በትግራይ ደርሷል ላለው በደል የቀደመ ታሪክን ጨምሮ በቅርቡ የፌዴራል መንግስት በትግራይ ባካሄደው ሕግ ማስከበር በተሰኘው ዘመቻ ደርሷል ያለውን ጠቅሷል፡፡

ማኅበሩ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የሶማሊያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ፋኖ እንዲሁም የተባበሩት ዐረብ ኤሜሬቶች ድሮን ተቀናጅተው 95 በመቶ የኦርቶዶክስ አማኝ ነው ባለው የትግራይ ሕዝብ ላይ ኅዳር 8፣ 2013 ‹‹ዘር ማጥፋት ሲያውጁ›› ሲኖዶሱ ቡራኬ ሰጥቷል በሚልም ወንጅሏል፡፡

የትግራይ ዓለም አቀፍ ካህናት ዘ ኦርቶዶክስ የተሰኘው ማኅበር ከኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋርጫለሁ ማለቱን ተከትሎ እስካሁን ድረስ ከሲኖዶሱ የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img