Sunday, October 6, 2024
spot_img

ታምራት ነገራ የታሠረበት አልታወቀም ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ታኅሣሥ 2፣ 2014 ― በትላንትናው እለት በፖሊስ ቀጥጥር ስር የዋለው የተራራ ኔትወርክ መሥራች እና የፖለቲካ ጉዳዮች አስተያየት ሰጪው ታምራት ነገራ ቀድሞ ወደ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ቢወሰድም አሁን የት እንዳለ እንደማይታወቅ ቤተሰቦቹ ገልጸዋል።

የሚሠራበት ተራራ ኔትወርክ እንዳስታወቀው ቤተሰቦቹ ቀድሞ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቢያቀኑም፣ ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ ተዛውሯል ተብለው ወደ ስድስት ኪሎ የሄዱ ቢሆንም፣ ወደዚያ እንዳልተዘዋወረ ተነግሯቸው ተመልሰዋል።

በዛሬው ዕለት በተመሳሳይ ቤተሰቦቹ ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ መምሪያ ያቀኑት ቤተሰቦቹ፣ ጉዳዩን የያዘው የኦሮሚያ ፖሊስ በመሆኑ ግሎባል አካባቢ በሚገኘው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ሄዳችሁ አጣሩ ተብለው እዚያም እንዳልመጣ ተነግሯቸዋል።

ይልቅኑም ወደ ቡራዩና ገላን ከተሞች ሄዳችሁ አጣሩ የተባሉት የታምራት ቤተሰቦች፣ በቡራዩ ከተማ በሚገኙ ሶስት ፖሊስ ጣቢያዎች በተጨማሪም ገላን ከተማ ወደ ሚገኘው ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ቢያቀኑም ማግኘት እንዳልቻሉ ነው የተገለፀው።

ከዚህ በተጨማሪም ሜክሲኮ የሚገኘውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ቢያናግሩም ጉዳዩን የያዘው የኦሮሚያ ክልል በመሆኑ እኛጋ አልመጣም የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

ታምራት ነገራ ትላንት ጧት በፖሊስ ከመኖሪያ ቤቱ ሲወሰድ፣ የጸጥታ አካላት የመኖሪያ ቤቱ እና ቢሮውን በመፈተሽ ለመረጃ ይፈለጋሉ ያሏቸውን የሚዲያ ዕቃዎች በሙሉ መውሰዳቸው ቢነገርም ለምን እንደታሰረ የተገለጸ ነገር የለም።

ከሰሞኑ ከታምራት ነገራ በተጨማሪ በኡቡንቱ ሚዲያ የሚሠራው አክቲቪስት እና የፖለቲካ አስተያየት ሰጪው እያስጴድ ተስፋዬ መታሠሩ መነገሩ አይዘነጋም።

በዛሬው እለት ደግሞ ሮሃ ቲቪ የተባለ የበይነ መረብ ብዙኃን መገናኛ መስራቿ እና በፕሮግራም አቅራቢነት የምትሠራው መዐዛ መሐመድ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሏ ተሰምቷል።

ዛሬ ጧት ወደ ሥራ እያቀናች በነበረበት ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው መዐዛ፣ ቤቷም ሆነ ቢሮዋ ላይ ፍተሻ እንዳልተደረገና ለጥያቄ እንፈልግልሻለን ተብላ መወሰዷ ነው የተነገረው።

በተከታታይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት እያስጴድ ተስፋዬ፣ ታምራት ነገራ እና መዐዛ መሐመድ ለምን እንደታሰሩ ፖሊስ ያሳወቀው ነገር ባይኖርም፣ ባለፉት ቀናት መታሰራቸውን የሚጠይቁ ድምጾች ከሰሞኑ በተለይ በፌስቡክ ሲስተጋቡ ቆይተዋል።

ከታሳሪዎቹ መካከል ከዚህ ቀደም ዐባይ ሚዲያ በተባለ የበይነ መረብ ብዙኃን መገናኛ በምትሠራቸው ቃለ ምልልሶች የምትታወቀው መዐዛ መሐመድ፣ ሮሃ ቲቪ የተባለውን ብዙኃን መገናኛ የከፈተችው በቅርቡ እንደነበር ተነግሯል፡፡

ታምራት ነገራ በበኩሉ ተወዳጅ በነበረችው በቀድሞ አዲስ ነገር ጋዜጣ ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ የጋዜጣውን መዘጋት ተከትሎ አስር ዓመት ገደማ በአሜሪካ ስደት ላይ ቆይቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ወደ አገር ቤት የተመለሰ ነው።

ሌላኛው ታሳሪ እያስጴድ ተስፋዬ በቀደመው ጊዜ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ነበር።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img