Thursday, November 28, 2024
spot_img

ብልጽግና ፓርቲ አገራዊ ምክክር አስፈላጊነት ላይ ተወያይቶ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ታኅሣሥ 1፣ 2014 ― ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትላንት ኅዳር 30፣ 2014 ባደረገው ስብሰባ የአገርን ህልውና ለማጽናትና ዴሞክራሲን ለማጎልበት አካታች አገራዊ ምክክር አስፈላጊ መሆኑን በማመን አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታውቋል፡፡

የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ፓርቲው አቅጣጫ ያስቀመጠለት አካታች አገራዊ ምክክር አገር በቀል የሆነ፣ በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያግዝ፣ ከሕዝቡ ባህልና ዕሴት ጋር የሚጣጣም፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በዘላቂነት ለማስከበር የሚረዳ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የታሰበው አገራዊ ምክክር እንዲሳካ ገለልተኛ የሆነና ብቃት ያለው አገራዊ ተቋም መመራት እንዳለበት ሥራ አስፈጻሚው እንዳመነበት የጠቀሱት ኃላፊው፣ ምክክሩ እንዲሳካና የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣም ብልጽግና ፓርቲ እንደመሪ ፓርቲ የሚጠበቀበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ማረጋገጡንም ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል የብልጽግና ፓርቲ ከሕወሓት ነጻ የወጡ አካባቢዎችን መልሶ ለማደራጀትና ለማቋቋም የተጀመረ ሥራ ላይ ግምገማ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ ሥራው በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

ለመልሶ ማቋቋምና ማደራጀት ሕዝቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ሥራ አስፈጻሚው ጥሪ ማቅረቡንም ነው ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img