Sunday, September 22, 2024
spot_img

የመከላከያ ሠራዊት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ መቐለ እንደሚገባ ሌተናል ባጫ ደበሌ ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ታኅሣሥ 1፣ 2014 ― ከሰሞኑ በሕወሓት የተያዙ በርካታ የአማራ እና አፋር ክልል አካባቢዎችን ከክልል የፀጥታ አካላት እና የአካባቢ ሚሊሻዎች ጋር በመሆን ማስለቀቁን ያስታወቀው የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ መቐለ ከተማ እንደሚገባ ሌተናል ባጫ ደበሌ ተናግረዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት የግንባታ ሥራዎች ኃላፊው ሌተናል ጀነራል ባጫ ይህን የተናገሩት በግንባር በተካሄደ መድረክ ላይ ተገኝተው መሆኑን የዋልታ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ሕወሓትን እስከ መጨረሻው በመቅበር ታላቁን የድል ዜና መቀሌ ላይ ሆነን እናበስራለን ያሉት ሌተናል ጀነራሉ፣ መከላከያ አስመዝግቧል ላሉት የእስካሁን ድል የልዩ ዘመቻዎች ኃይል፣ የሪፐብሊክ ጥበቃ ኃይል እና የአየር ወለድ አባላት ‹‹በጭንቅ ላይ ያለች አገርን ችግር የፈቱ›› ሲሉ አወድሰዋቸዋል፡፡

አንድ ዓመት በተሻገረው የፌዴራል መንግስት እና የሕወሓት ኃይሎች ጦርነት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር መጨረሻ መቐለን በመቆጣጠር ለወራት የቆየ ሲሆን፣ በሰኔ ወር መገባደጃ መንግሥት ያወጀውን የተናጠል የተኩስ አቁም ተከትሎ ለቆ መውጣቱ አይዘነጋም፡፡

ይህንኑ ተከትሎ መቐለን የተቆጣጠረው የሕወሓት ኃይል፣ ወደ አጎራባች አፋር እና አማራ ክልሎች በመግፋት እስከ ሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ድረስ ዘልቆ እንደነበር ይታወቃል፡፡

በመከላከያ ሠራዊት እና በሕወሓት መካከል በቅርብ ጊዜያት በነበረው ውጊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወደ ግንባር እንዲዘምቱ ያደረገ ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ግንባር መዝመት ተከትሎ የፌዴራል የፀጥታ ሀይሎች በአሁኑ ወቅት ደሴ፣ ኮምቦልቻ እና ሐይቅ ከተሞችን ይዘዋል፡፡ ነገር ግን በሕወሓት ኃይሎች በኩል ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ቴሌቪዥን ቀርበው ይዘናቸው የነበርናቸውን ከተማዎች ተሸንፈን ሳይሆን ‹በወታደራዊ ውሳኔ ያደረግነው ነው› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img