Saturday, November 23, 2024
spot_img

የሕወሓት ቃል አቀባዩ ዋንኛ አላማቸው “የሕዝባችንን ደኅንነትና ሕልውና በአስተማማኝ መልኩ ማረጋገጥ ነው” ሲሉ ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 30፣ 2014 ― የሕወሓት ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ እያካሄዱት ባለው ጦርነት ዋንኛ አላማቸው “የህዝባችንን ደህንነትና ህልውና በስተማማኝ መልኩ ማረጋገጥ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ የሕወሓት ኃይሎች ድንበር ተሻግረው የያዟቸው የአፋር እና አማራ ክልል አካባቢዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ በቴሌቭዥን ቀርበው በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ የያዟቸው ቦታዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር መዋላቸው “የጦር ስትራቴጂን ያማከለ የቦታ ለውጥ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ በትላንትናው እለት ከትግራይ ቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ “ጠላት” ሲሉ የጠሩትን የፌዴራል መንግስት ሃይል “ለመደምሰስ የምናደርገው እንቅስቃሴ ከስልጣን ጥማት ወይንም ለሌላ ተደራቢ አላማ ያለው ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም” ብለዋል።

ይዘዋቸው የነበሩትን ከተማዎች ለምን እንደለቀቁም ተጠይቀው “የህዝባችንን ህልውና ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆነ ማስተካከያዎችን በየግዜው ስናደርግ ቆይተናል አሁንም ቢሆን የደረስንበት ደረጃ ላይ ሆነን ጠላት ከቀድሞ የወንጀል ሸሪኮቹ ጋር ሁሉ በማበር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ስለነበረ ይህን የጥፋት እንቅስቃሴ ለማምከንና የጀመርነውን ጠላትን የማስወገድ እንቅስቃሴ በተሻለ ለማሳለጥ የሚያችሉ ወታደራዊ ውሳኔዎች ናቸው””ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ባለፉት ሁለት ሳምንታት የሕወሓት ኃይሎች ይዘዋቸው የነበሩ የሰሜን ሸዋ እና የአፋር አካባቢዎችን ጨምሮ የደሴ እንዲሁም ኮምቦልቻ ከተሞችን ተቆጣጥረዋል።

አቶ ጌታቸው በበኩላቸው የመንግስት የፀጥታ ኃይል “እንቅስቃሴያችንን ለማስተጋጎል ያደረገው እንቅስቃሴ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በተለይም ወደ ውስጥ ዘልቆ ገብቶ የነበረውን ሀይላችንን ትጥቅና ስንቅ አቅርቦትን ለማስተጓጎል ያደረገው እንቅስቃሴ ነበር፣ ይህን ተከትሎ መሰናክሎችን ለመበጣጠስ፣ ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስና የተጀመረውን ግብአተ መሬት የማፋጠን ስራ ለመስራት ያስችል ዘንድ የተደረገ ነው” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል እርምጃውን የወሰዱት በሃያላን ሃገሮች ተፅእኖ ነው ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ቃል አቀባዩ፣ በቀጥታ ሳይመልሱ ስለ በቻይና፣ በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እና አሜሪካ ላይ ያላቸውን አቋም አስረድተዋል።

“ቻይናዎች በመሳሪያ በሌሎችም ዐቢይን ይደግፉታል” ያሉት ጌታቸው፣ በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥም ድምፅን በድምፅ የመሻር መብታቸውን በመጠቀም ማእቀብ እንዳይጣል በሃገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መገባት የለበትም በሚል ሰበብ መንግስትን ይከላከላሉ ብለዋል።

አሜሪካን በተመለከተ ደግሞ “ለመረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው” ሲሉ የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ “አንዴ ዐቢይ አደገኛ ነው ወደ አልሆነ ጥፋት ሃገሪቱን ይዞ እየሄደ ነው ይላሉ፣ ትንሽ ቆይተው ደግሞ ህወሃት አዲስ አበባ ከገባች ሃገር በደም ትታጠባለች ይላሉ፣ ይህ ሁሉ ተረት ከየት እንደሚመጣ አላውቅም በእኔ ግምት አሜሪካ ሕወሃት ስልጣን ተቆጣጠሮ ፈላጭ ቆራጭ እንዲሆን ፍላጎት የላትም፣ ምንም እንኳን እኛ ስልጣን የመያዝ ፍላጎት እንደሌለን ብንነግራቸውም” ብለዋል።

አቶ ጌታቸው አያይዘውም “ዐቢይን እስከአፍንጫው እያስታጠቀች” ነው ያሏት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን፣ “አሜሪካ ማስቆም ብትፈልግ ትችል ነበር ይህ ወንጀለኛ ሊወገድ የሚገባው ስርዓት እድሜው እንዲረዝም አስተዋፅኦ እያረጉ በተቃራኒው የትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና በደል ከማጋለጥና አለም እንዲያውቀው ከማረግ ያለፈ የዲፕሎማሲ ድጋፍ ውጪ ሌላ የማይረዱን አካላት ተመለሱ ስላሉን ልንመለስ አንችልም ይህ ሊታውቅ ይገባል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img