አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሚያዝያ 18፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ይህን ስጋቱን የገለፀው ባዘጋጀው በወቅታዊ የአገሪቱ የደኅንነት ስጋቶች ሰነድ ላይ ነው። ዘ ቲ ኤፍ አይ ስቴሽን ይዞት የወጣው የፓርቲው ይፋ ያልሆነ ሰነድ እንደሚያመለክተው ፓርቲው በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ከፍተኛ እና ውስብስብ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋቶች ተጋርጠውባታል በማለት የተለያዩ ጉዳዮችን ዘርዝሯል።ከነዚህ መካከል አንደኛው ጽንፈኝነት ነው ያለው ኢዜማ፣ በተለይ በሁለቱ የአገሪቱ ትላልቅ ሃይማኖቶች እስልምና እና ክርስትና ውስጥ አለ ያለውን “ጽንፈኝነት” አብራርቷል።ፓርቲው በሁለቱም ሃይማኖቶች አካባቢ አለ ያለውን ጽንፈኝነት ሲያስረዳ በእስልምና አካባቢ “በእስልምና አክራሪዎች ቀስቃሽነት የእስልምና እምነት ተከታዮች በሚበዙባቸው የተለያዩ ቦታዎች ላይ የአክራሪ አስተምህሮዎችን በወጣቱ ላይ በማስረጽ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት የሚሳተፉበትን ሁኔታ እየፈጠሩ ይገኛል ብሏል።በሌላ በኩል የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት አክራሪነት እየተስፋፋ እየመጣ ነው ያለው ፓርቲው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት በተለያየ አቅጣጫ የጥቃት ኢላማ ተደርጋለች የሚለው እሳቤ በበርካታ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ እየተቀነቀነ እንደሚገኝ ጠቁሟል።ይህ አዝማሚያ የእምነቱ ተከታዮች እምነቱን ከጥቃት ለመጠበቅ በሚል ሊያሰባሰስብ የሚችልም ነው ብሎታል። ይህ ዐይነቱን አዝማሚያ በቅርብ ጊዜ የመጡት እናት እና ነጻነት እና እኩልነት የተባሉ ፓርቲዎች እምነት ተኮር በመሆናቸው የሃይማኖት ጽፍኝነትን ፖለቲካዊ ቅርጽ እንዲዝ የማድረግ አቅም እንዳላቸው በመግለጽ፣ እነዚህን ፓርቲዎች በቅርበት መከታተል ያስፈልጋል ብሏል፡፡ ፓርቲው ይህን ማለቱን ተከትሎ ሁለቱም ፓርቲዎች እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ የሰጡት ምላሽ የለም፡፡