Sunday, September 22, 2024
spot_img

ቦርዱ ከ53 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ጠቅላላ ጉባኤ ያደረጉት 2 ብቻ ናቸው አለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ኅዳር 29፣ 2014 ― በኢትዮጵያ በሕጋዊነት ከተመዘገቡ 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከምርጫ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ ያደረጉት ሁለት ፓርቲዎች ብቻ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

ከቦርዱ ኮሚዩኒኬሽን ክፍል ሰምቻለሁ ብሎ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር እንደዘገበው፣ ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ ያደረጉት ሁለት ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (አብአፓ) ናቸው።

አብአፓ ነሐሴ 27፣ 2013 ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤው የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻሉን፣ የጉባኤውን አባላት ቁጥር ከፍ ማድረጉን እና የአዲስ አመራሮች ምርጫ ማካሄዱን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሄር መናገራቸው በዘገባው ተመላክቷል፡፡

ጠቅላላ ጉባኤውን ባለፈው መስከረም ወር ያደረገው ኢዜማም የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ አሻሽሏል። ምርጫ ቦርድ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ባሳለፈው ውሳኔ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ከማካሄድ ባለፈ የመተዳደሪያ ደንባቸውን እንዲያስተካክሉ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። 

ኢዜማ በመስከረሙ ጠቅላላ ጉባኤው ተወያይቶ በአብላጫ ድምጽ ያጸደቀው ሌላው ጉዳይ፤ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ የአብረን እንስራ ጥያቄን ነበር። ይህን የፓርቲውን ውሳኔ ተከትሎ የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ን ጨምሮ የተወሰኑ የኢዜማ አመራሮች የተለያዩ መንግስት ተቋማትን የመምራት ኃላፊነት ተረክበዋል። 

ምርጫ ቦርድ ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ባሳለፈው ውሳኔ፤ ከምርጫ ህግ መሻሻል በኋላ በአዲስ መልክ የተመዘገቡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያደርጉ ወስኖ ነበር። ሆኖም ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ በመቃረቡ፤ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄዱ ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለቦርዱ ጥያቄ አቅርበዋል።  

ቦር እስካሁን ጠቅላላ ጉባኤ ያላደረጉትን ሁሉንም ፓርቲዎች፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተጠናቀቀ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጉባኤያቸውን እንዲያከናውኑ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ውሳኔ ማስተላለፉ ተነግሯል፡፡   

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img