አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ኅዳር 29፣ 2014 ― የሕወሓት ኃይል ተቆጣጥሮት በነበረው ደሴ ከተማ የሚገኘውን የደሴ ሪፈራል ሆስፒታልን ሙሉ ለሙሉ መዝረፉ እና መውሰድ የማይችለውን ደግሞ ማውደሙ ተነግሯል፡፡
ይህንኑ የሆስፒታሉ ጊዜያዊ አስተባባሪ ጌታቸው መታፈሪያ እንደነገሩት አሐዱ ሬድዮ ዘግቧል፡፡
ቡድኑ መድሃኒትን ጨምሮ ትላልቅ የህክምና መሳሪያዎችን ዘርፎ መውሰዱን የገለጹት ኃላፊው፣ በተለይ በቅርቡ ተመርቆ በሆስፒታሉ ወስጥ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረውን የኦክስጅን ማምረቻ ሙሉ ለሙሉ መዝረፉን ገልጸዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም ቡድኑ በሆስፒታሉ በቅርቡ ተገዝተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ አልጋዎችን ደግሞ አውድሟቸዋል ብለዋል፡፡
ታጣቂዎቹ በተመሳሳይ መውስድ ያልቻሏቸውን መድሃኒቶች ጥቅም እንዳይሰጡ አድርገው መሄዳቸውም የተነገረ ሲሆን፣ የሆስፒታሉን ጀኔነተር ነዳጅ ዘርፎ በመውሰድና ሆስፒታሉ ነዳጅ እንዳያገኝ በመከልከል መትረፍ የሚችሉ ህመምተኞች እንዲሞቱ ማድረጋቸውም ተገልጧል፡፡