- የወረዳው ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ጀባሞ በወረዳቸው ውስጥ ዕርምጃ የተወሰደባቸው አብዛኞቹ ሆቴሎች ከሕወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ በመጠርጠራቸው መሆኑን ገልጸዋል
አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ኅዳር 29፣ 2014 ― በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ አትላስ አካባቢ የሚገኘው ‹‹ሳፋየር አዲስ ሆቴል›› በግልጽ ባልተነገረ ምክንያት መታሸጉ ተሰምቷል፡፡
ሪፖርተር የሆቴሉን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ወርቁን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ሳፋየር አዲስ ከሐሙስ ኅዳር 23፣ 2014 ጀምሮ ታሽጓል፡፡
ሥራ አስኪያጁ ሆቴሉ በምን ምክንያት እንደታሸገ ከመንግሥት አካላት የተደረገላቸው ገለጻ እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡
ባለፉት ሦስትና አራት ወራት ውስጥ ሆቴሉ ለአራት ጊዜ ፍተሻ እንደተደረገበትና የመጨረሻው ፍተሻ ከመታሸጉ ሁለት ቀናት በፊት ማክሰኞ ኅዳር 21፣ 2014 እንደነበር አቶ ዮናስ መግለጻቸው ተመላክቷል፡፡ ‹‹በሁሉም ፍተሻ ምንም ነገር አልተገኘም፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ይህን የሚያረጋግጥ ፊርማ የፈተሹት አካላትና የሆቴሉ አስተዳዳር መፈረማቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡
አቶ ዮናስ ሆቴሉ ከመታሸጉ በፊት ማስጠንቀቂያ አለመሰጠቱን ተናግረው፣ አሁንም ቢሆን ከመንግሥት በኩል ምክንያቱ እስከሚነገራቸው እየጠበቁ መሆኑን በማስረዳት፣ በፍተሻው ጊዜ ምንም ስላልተገኘባቸው በቶሎ ይከፈታል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
ሳፋየር አዲስ ሆቴልን ያሸገው የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በበኩሉ፣ ዕምርጃው የተወሰደው በወረዳው በተዋቀረው ግብረ ኃይል አማካኝነት ጥናት ተደርጎ መሆኑን ማስታወቁን የጋዜጣው ዘገባ ያመለክታል፡፡ የወረዳው ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ጀባሞ፣ ሳፋየር አዲስ የታሸገበትን ምክንያት ከመናገር ተቆጥበው፣ ወረዳው ውስጥ ‹‹በወቅታዊ ሁኔታ›› ዕርምጃ የተወሰደባቸው አብዛኞቹ ሆቴሎች ‹‹በአሸባሪነት ከተፈረጀው ሕወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው፣ እንዲሁም ድጋፍ ያደርጋሉ›› ተብሎ በመጠርጠራቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አንዳንዶቹ ሆቴሎች ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ መገኘቱንም ሥራ አስፈጻሚው አክለው ገልጸዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት እስካሁን 100 ገደማ የሚሆኑ እንደ ሆቴል፣ ባርና ሬስቶራንት ያሉ ቤቶች ላይ የማሸግ ዕርምጃ እንደተወሰደ ያስታወቀ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ከወራት በፊት የታሸጉት ካሌብ፣ አክሱምና ሐርመኒ ሆቴሎች ይገኙበታል፡፡ በወረዳው ባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ 12 ቤቶች መታሸጋቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ዕርምጃው የተወሰደባቸው ከፀጥታ አካላት በመጣ ትዕዛዝ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ባለ አራት ኮከቡ ሳፋየር አዲስ ሆቴል ከ2009 ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፣ 180 ሠራተኞች፣ 130 የእንግዳ ክፍሎችና የስብሰባ አዳራሾች እንዳሉት ተነግሯል፡፡