አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ኅዳር 28፣ 2014 ― አክቲቪስት እና የፖለቲካ አስተያየቶችን በመስጠት የሚታወቀው እያስጴድ ተስፋዬ በዛሬው እለት በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ታውቋል።
እኩለ ቀን ሰባት ሰአት ገደማ በቁጥጥር ስር የዋለው እያስጴድ፣ ቤቱ ተበርብሮ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ወደ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዱ ነው የተሰማው።
የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ አባል እና በቅርብ ጊዜያት ኡቡንቱ በተባለ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን የፖለቲካ ጉዳዮችን የሚያቀርበው እያስጴድ፣ የመንግስትን ሥልጣን በያዘው በገዢው ብልጽግና ፓርቲ ላይ ትችት በመሰንዘር ይታወቃል።
ይህንኑ ተከትሎ በመንግስት ደጋፊዎች ዘንድ በቁጥጥር ስር ይዋልልን የሚሉ ድምጾች ሲሰሙበት ነበር።
ነገር ግን የእያስጴድ ተስፋዬ የእስር ምክንያት ከፖለቲካ አስተያየቶቹ ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።