አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ኅዳር 25፣ 2014 ― በኤርትራ መዲና አስመራ የአሜሪካ ኤምባሲ በዋሺንግተን የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ የኤርትራ ወታደሮችን የትግራይ ጦርነት ተሳትፎ በተመለከተ ተከላክሎ ያወጣውን መግለጫ ውድቅ አድርጎታል፡፡
በዋሺንግተን የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ የአሜሪካ ሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት አባል የሆኑት ብራድ ሼርማን የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል እርዳታ እንዳይዳረስ አድርገዋል በሚል የአገራቸውን ወታደሮች ጣልቃ ገብነት መጠየቃቸውን ተከትሎ ይህንኑ በመቃወም ሌላ መግለጫ አውጥቷል፡፡
ኤምባሲው በመግለጫው፣ የሕዝብ እንደራሴ አባሉ ወታደሮቹ በትግራይ እርዳታ አስተጓጉለዋል በማለት የሰጡትን አስተያየት ያለ ማስረጃ የተሰጠና አስደንጋጭ ነው ብሎታል፡፡ አያይዞም ኤርትራ በኢትዮጵያ እርዳታ እንዳይዳረስ እንቅፋት ሆና እንደማታውቅ የገለጸ ሲሆን፣ የእርዳታ አቅርቦት መዳረሻዎች ከአገሪቱ ጋር ግንኙነት እንደሌለውም አስታውቋል፡፡
በአንጻሩ የአስመራ ኤምባሲን ማስተባበያ ተቃርኖ መግለጫ ያወጣው በአስመራ የሚገኘው አሜሪካ ኤምባሲ፣ የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ እርዳታ እንዳይዳረስ እንቅፋት መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ፈጽመዋቸዋል ያለውን ሌሎች የመብት ጥሰቶችን ዘርዝሯል፡፡
ኤምባሲው በወታደሮቹ በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል ብሎ ከዘረዘራቸው የመብት ጥሰቶች መካከል የአስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ሕጻናት ላይ ግድያን ጠቅሷል፡፡ ኤምባሲው ይኸው የመብት ጥሰት በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የተሰነደ ስለመሆኑ ገልጧል፡፡
የአሜሪካ ኤምባሲ በመግለጫው ማሳረጊያ በትግራይ አድርጎታል ያለው የተሳሳተ ወታደራዊ ተሳትፎ ቀጣናውን እያመሰ እንዲሁም ቀድሞውኑ በአደገኛ ሁኔታ ላይ የነበረውን የሰብአዊ ሁኔታም ማባባሳቸውን በመጥቀስ፣ ወታደሮቹ በአስቸኳይ የኢትዮጵያን መሬት ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል፡፡