አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ኅዳር 25፣ 2014 ― በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን መካነ-ሠላም ከተማ የሚገኙ ከሰሜን ወሎ አካባቢ የተፈናቀሉ 2 ሺሕ 339 ተፈናቃዮች ችግር ላይ መሆናቸው ተነግሯል።
ከሰሜን ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ወደ መካነ-ሠላም ከተማ ካቀናን ከአንድ ወር በላይ አስቆጥረናል የሚሉት ተፈናቃዮቹ፣ መሠረታዊ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ችግር ላይ መሆናቸውን እንደተናገሩ አዲስ ማለዳ ዘግቧል።
ተፈናቃዮቹ ከአላማጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ መርሳ እና ሌሎች የሰሜን ወሎ አካባቢዎች የመጡ ሲሆን፣ አሁን ላይ በመካነ-ሠላም ትምህርት ቤት እንደሚገኙ የተፈናቃይ ኮሚቴ አባል የሆኑት አብዱ እንድሪስ ገልፀዋል።
አብዱ እንድሪስ በጦርነቱ ምክንያት ከአካባቢያቸው ተሰደው ላለፉት ሦስት ወራት በደሴ ከተማ የቆዩ ቢሆንም፣ ከጥቅምት 20፣ 2014 ወዲህ ግን ወደ መካነ-ሠላም ከተማ እንዳቀኑ ነው የገለጹት።
ወደ መካነ-ሠላም ከተማ ካቀናን ከአንድ ወር በላይ አስቆጥረናል የሚሉት አብዱ፣ እስከ አሁን አንድ ጊዜ ብቻ 12.5 ኪሎ ዱቄት እንደተረዱና ከዚያ ወዲህ ግን ድጋፍ ባለማግኘታቸው የምግብ፣ የመኝታ፣ የአልባሳት፣ የውኃና የመብራት ችግር እንዳጋጠማቸው ነው ያመላከቱት።
ከኹሉም በላይ የውኃ ዕጥረት በመኖሩ በተለይም ሴቶችና ሕፃናት ችግር ላይ ናቸው የሚሉት አብዱ እንድሪስ፣ እስካሁን ኹለት ቦቲ መኪና ውኃ ብቻ እንዳገኙና የመጠጥ ውኃ ችግር ቢኖርባቸውም በድጋሚ ማግኘት አለመቻላቸውን መግለጻቸው በዘገባው ተመላክቷል።
በጉዳዩ ላይ የተናገሩት የደቡብ ወሎ አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ኃላፊ መሳይ ማሩ፣ ተፈናቃዮቹ ያቀረቡት ቅሬታ እውነት መሆኑን አረጋግጠው፣ ችግሩን ለመቅረፍ ምን እየሠሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በመካነ-ሠላም ከተማ በጠቅላላው 10 ሺሕ 171 ተፈናቃዮች እንዳሉ የገለጹት ኃላፊው፣ 2 ሺ 339 ሰዎች፣ በቦረና በሚገኙ ኹለት ትምህርት ቤቶች፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በዘመድ ቤትና በኪራይ ቤት እንደሚኖሩና ድጋፍ ለማዳረስ ስለተቸገሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትብብር እንዲያደርግላቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።