አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ኅዳር 25፣ 2014 ― የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ምክር ቤት የፌዴራልና የክልል መንግስት ያወጀውን የአስተቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመተላለፍ በከተማው የጥይት ተኩስ እና ኢ መደበኛ ወታደራዊ ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡
ይህ ትክክል አለመሆኑን ደጋግሞ ማሳወቁን ያስታወሰው የጸጥታ ምክር ቤቱ፣ መደበኛ ያልሆነ ወታደራዊ ስልጠና በሚወስዱ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡
የከተማው ጸጥታ ምክር ቤት ከዚህ በተጨማሪም በከተማው ጥይት ተኩስ የሚተኩሱ ግለሰቦች ላይ በተመሳሳይ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በማሳሰብ እርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡
በድርጊቱ ላይ የሚሳተፉ ሰዎችን ያስጠነቀቀው ምክር ቤቱ፣ የከተማው ሕዝብ እንደተለመደው መረጃ በመስጠት እንዲሁም የሚታዩ ኢ-መደበኛ እንቅስቃሴዎችን፣ ስውር እንቅስቃሴዎችን በመጠቆምና በማስቆም ትብብር እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ምክር ቤት ከዚህ ቀደም ስምሪት ከተሰጠው የፀጥታ ሃይል ውጭ በከተማችን ማንኛውንም አይነት የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ መከልከሉ ይታወሳል፡፡