አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሚያዝያ 18፣ 2013 ― የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና ክልሉን የሚመራው ፓርቲ ብልጽግና የሦስተኛ ሩብ ዓመት ግምገማውን በአዳማ ከተማ እያካሄደ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡የክልሉን ርእሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ ዐብዲሳ እና የጨፌ ኦሮሚ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተውበታል በተባለው ግምገማ ላይ የክልሉ የሰላም ሁኔታ፣ የልማት ሁኔታ እንዲሁም የቀጣዩ ወር ምርጫ ዝግጅት ይገመገማል ነው የተባለው፡፡ የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ኃላፊ አቶ ግዛቸው ገቢሳ ለሸገር እንደተናገሩትም ለመጪው ምርጫ የጸጥታው መዋቅር የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ተጠብቋል፡፡ የአሁኑ ግምገማ በክላስተር ደረጃ የተገመገሙ ሥራዎች ወደ ክልል መጥተው የመደምደሚያ ግምገማ እንደሚደረግበት በተነገረው ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚደረግ ነው ተብሏል፡፡ለሁለት ቀናት የሚቆየውን ግምገማ በአመራሮቹ በኩል እያደረገ በሚገኘው የኦሮሚያ ክልል፣ ለመጪው ወር ምርጫ 12 ሚሊዮን ያክል መራጮች ቢመዘገቡም፣ በተለይ የፀጥታ ችግር አለባቸው በሚባሉት በምእራብ፣ ምሥራቅ፣ ሆሮ ጉድሩ እና ቄለም ወለጋ በጸጥታ ስጋት ሰበብ አንድም የምርጫ ጣቢያ እንዳልተከፈተባቸው ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡